በሰሜን ኔዘርላንድስ የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ናት:: "ጊቱርን" መጠሪያ ስሟ ሲሆን፤ "መንገድ የለሽ" የሚል ስያሜን ደግሞ አግኝታለች::
ከተማዋ ይህን ስያሜ ልታገኝ የቻለችዉ ለተሽከርካሪዎች የሚሆን ምንም አይነት መንገድ ስለሌላት ነው::
በጊቱርን ብቸኛዉ የጉዞ አማራጭ በከተማዋ ዉሃ መንገዶች ላይ ያሉት ጀልባዎች እና ብስክሌቶች ናቸው:: በእግር መሄድ ደደሞ ሶስተኛዉ አማራጭ::
በኔዘርላንዷደ ጊቱርን ከተማ ወደ ስራ ለመሄድ ይሁን የዕለት ተዕለት ስራን ለመከወንም ከ 500 - 600 በሚጠጉት የከተማዋ ጀልባዎች መጠቀም ገዴታው ነው::
ከተለያዩ የዓለም ሃገራት ወደ ጊቱርን የሚገቡ ጎብኚዎችም ቢሆን መንገድ የለምና መኪኖቻቸዉን መጠቀም አይችሉም::
በጊቱርን የሚገኙት የዉሃ ላይ መንገዶች (ቦዮች) ከጥንት ጀምሮ በምህንድስና ባለሙያዎች እገዛ የተሰሩ ቦዮች ናቸው::
መንገዶቹ ከተማዋን በአራቱም አቅጣጫዎች የሚያገናኙ መሆናቸውንም ከሊትል ቢግ ስቶሪ (Little Big Story) የተገኘዉ መረጃ ይጠቁማል::
በከተማዋ ዉሃማ መንገዶች ላይ የተገነቡ 176 ድልድዮችም ለጀልባዎች እና እግረኞች መሸጋገሪያነት ያገለግላሉ::
ድልድዮቹ የትራፊክ መጨናነቅ ሲኖር እንደሁኔታው የሚዘጉ እና የሚከፈቱ በመሆናቸው የድልድይ ጠባቂዎች (Bridge guards) አሏቸው::
ሌሎች ከተሞች የእሳት አደጋን ለመከላከል የእሳት አደጋ መኪኖች እንዳሏቸው ሁሉ ጊቱርን ደግሞ የእሳት አደጋ ጀልባዎች አሏት::
የእሳት አደጋ ጀልባዎች እና ሰራተኞቻቸዉ ተግባር ደግሞ የእሳት አደጋን እና በጀልባ የመስጠም አደጋን መከላከል ነው::
በየአመቱ በአማካይ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ የተለያዩ አለም ሃገራት ጎብኚዎች ጊቱርን ከተማን ይጎበኛሉ::
በዘለቀ አወቀ