የህፃን ባምላክ (ኬብሮን) ገዳዮች የሞት ፍርድ ተወሰነባቸው

6 Hrs Ago 1542
የህፃን ባምላክ (ኬብሮን) ገዳዮች የሞት ፍርድ ተወሰነባቸው

በህፃን ባምላክ (ኬብሮን) በገደሉ ግለሰቦች ላይ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬደዋ ምድብ ችሎት የሞት ቅጣት መወሰኑን አስታወቀ።

1ኛ ተከሳሽ ሀና በየነ ገብረዮሀንስ እና 2ኛ ተከሳሽ ብሩክ አለሙ ተሰማ በህፃን ባምላክ (ኬብሮን) ግርማ ላይ በፈፀሙት የግድያ ወንጀል የሞት ቅጣት መተላለፉን በፍትህ ሚኒስቴር የድሬዳዋ ቅርንጫፍ አቃቤ ህግ በተለይ ለኢቲቪ በገለጹት መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

ተከሳሾች በአንደኛ ክስ በ1996 የወጣውን የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና 539 (ሀ) በጋራ በመሆን ሰውን ለመግደል በማስብ ጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከለሊቱ 5፡ ዐዐ ሰዓት ገደማ በድሬዳዋ ከተማ 04 ቀበሌ ልዩ ቦታው ካባ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የመኖርያ ቤታቸው ውስጥ የ1ኛ ተከሳሽ ልጅ እና የ2ኛ ተከሳሽ የእንጀራ ልጅ የሆነችውን የግል ተበዳይ ህፃን ባምላክ (ኬብሮን) ግርማን ስለታማ ባልሆነ ቁስ አካል በመደብደብ ለከፍተኛ አካላዊ ጉዳት ከመዳረጋቸውም በላይ  ህፃኗን በማፈን አየር እንድታጣ እና ህይወቷ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲያልፍ ያደረጉ መሆኑ በክሱ ተመላክቷል።

በሁለተኛ ክስ በ1996 የወጣውን የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና 375 (ሀ) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም የግል ተበዳይ አባት እውነተኛ ወላጅ አባቷ አቶ ግርማ አበጋዝ ሳይሆን 2ኛ ተከሳሽ እንደሆነ ሀሰተኛ የዲኤንኤ ማስረጃ በማሰራትና ለፍርድ ቤት ሕጋዊ ክርክር ለማስረጃነት በማዘጋጀት ሀሰተኛ ሰነዶችን በመፍጠር ወንጀል ተከሰዋል፡፡

በሶስተኛ ክስ በ1996 የወጣውን የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና 585(2) (ሀ) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ ጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ወደ ወላጅ አባቷ እንዳትሄድ፣ በፍርድ በወንድሟ ላይ አልመሰክርም እንዳትላቸው ለማባበል እና ለማስፈራራት፤ ታማለች ጸበል እያስጠመቅናት ነው በማለት ትምህርት እንድታቋርጥ አድርገው ከሰው እንዳትገናኝ ቤት ውስጥ ቆልፈውባት ያስቀመጧት በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ከሕግ ውጪ ሰዎችን ይዞ ማቆየት ወንጀል ተከሰዋል፡፡

በአራተኛ ክስ ደግሞ በ1996 የወጣውን የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) ሀ እና 590(1) (ሐ) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ ተከሳሾች በጋራ በመሆን በሟች ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ሻወር በምትወስድበት ጊዜ ቪድዮ ቀርፀው ከግንቦት 2014 ዓ.ም ህይወቷ እስካለፈበት ጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እኛ የምንልሽን የማትሰሚ እና ከእኛ ጋር አርፈሽ ካልተቀመጥሽ፣ አባቴ እና ወንድሜ ጋር እሄዳለሁ ብለሽ የምታስቸግሪን ከሆነ ይሄንን ቪዲዮ ነው ለህዝብ አሳይተን ጉድሽን የምናፈላው እያሉ ሊጠብቋት፣ ሊንከባከቧት እና ፍቅር ሊሰጧት ሲገባቸው የተለየ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በማስፈራራት በህፃኗ ነፃነት ጣልቃ ገብተው ከወላጅ አባቷ እና ከወንድሟ ጋር እንዳትገናኝ ያደረጓት በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ከባድ የማስገደድ ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ከባድ የግድያ ወንጀል ተከሰው በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ከተደረገ በኃላ ድርጊቱን እንዲከላከሉ መደረጉም ተጠቁሟል።

ተከሳሾች በህግ የተሰጣቸውን ራሳቸውን የመከላከል መብት ባለመጠቀማቸው እንዲሁም ድርጊቱን መፈፀማቸው ዐቃቤ ሕግ በሰውና በሰነድ ማስረጃ በማረጋገጡ ችሎቱ በዛሬው ውሎ ተከሳሾቹ በሞት እንዲቀጡ ወስኗል።

በቴዎድሮስ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top