Search

ዓለም እንዴት እርስ በርሳቸው የሚቃረኑት ድርቅ እና የባሕር ወለል መጨመርን በአንድ ጊዜ አስተናገደች?

22 ዓመታት ጥናት የገለጠው የፕላኔታችን ቀጣይ መከራ። ዓለም እንዴት እርስ በርሳቸው የሚቃረኑት ድርቅ እና የባሕር ወለል መጨመርን በአንድ ጊዜ አስተናገደች?

የምድር 75 በመቶው ውኃ ነው፤ ከዚህ በተቃረነ ሁኔታ ደግሞ ዓለም በመጠጥ ውኃ እጥረት እና በድርቅ እየተሰቃየች ነው። ለመሆኑ ይህ የሚቃረን እውነታ እንዴት የሰው ልጆች መኖሪያ በሆነችው ምድር ላይ ሊከሰት ቻለ?

በአየር ንብረት ለውጥ እና ሳይንሳዊ ጉዳዮች ላይ ለኤን.. የምትጽፈው ዴኒስ ቾው በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ሳይንሳዊ ሀተታ አቅርባለች። 

የከርሰ ምድር ውኃ ያለ አግባብ መባከን ለድርቅ መባባስ እና ለከፍተኛ የሙቀት መጠን መጨመር ምክንያት መሆኑን በጥናት መረጋገጡን ታወሳለች።

የከርሰ ምድር ውኃ መሟጠጥ የምድርን ሙቀት በመጨመር የበረዶ ግግሮችን ማቅለጡ የፕላኔቷን ጠቅላላ ውኃ ወደ ውቅያኖሶች እየወሰደው የባሕር ወለል ከፍታ እየጨመረ መምጣቱን ትጠቅሳለች።

ይህ ሁኔታ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ ለማግኘት አስቸጋሪ ከማድረጉም በላይ የእርሻ መሬት በድርቅ ምክንያት ወደ ሸክላነት እየተለወጠ በመምጣቱ በግብርና ባደጉ አካባቢዎች ጭምር የምግብ ፍጆታን ማሟላት ስጋት እየሆነ መጥቷል።

ከጥናት አቅራቢዎቹ አንዱ የሆኑት በአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የዘላቂነት ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር ጄይ ፋሚግሊቲ ናቸው፤ ፕሮፌሰሩ ሰዎች ሰብል ለማምረት ብዙ ውኃን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጠቀሙ ጠቅሰው፣ የአሁኑ የውኃ አጠቃቀም ልማድ ካልተቀየረ በአጠቃላይ የውኃ ፍላጎት እና የምግብ ዋስትና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ያስጠነቅቃሉ።

ተመራማሪዎቹ በጥናቱ ላይ እንደጠቀሱት የችግሩን አሳሳቢነት ለማኅበረሰብ፣ ለመሬት ሀብት ሥራ መሪዎች እና በዓለም ዙሪያ ላሉ ውሳኔ ሰጪዎች ማሳሳብ ይገባል።

ተመራማሪዎቹአህጉራት እየደረቁ ነው፣ ጨዋማ ያልሆነ ውኃ በቀላሉ የሚገኝበት ሁኔታ እየቀነሰ ነው፣ የባሕር ወለል መጨመርም እየተፋጠነ ነውበማለት የችግሩን አሳሳቢነት አክለዋል።

ባለፈው ሳምንትሳይንስ አድቫንስበተባለው መጽሔት ላይ የታተመው ይህ ጥናት ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ሐይቆች፣  የከርሰ ምድር የውኃ ምንጮች እና በአፈር ውስጥ የሚገኘው እርጥበት አዘል የውኃ ምንጭ ላይ የመጡ ለውጦችን ገምግሟል።

ተመራማሪዎቹ የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ የምድርን የተፈጥሮ የውኃ ዑደት የሚያውኩ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ይህም እርጥበት በመሬት፣ በውቅያኖሶች እና በከባቢ አየር መካከል የሚዘዋወርበትን መንገድ አዛብቷል ብለዋል።

ተመራማሪዎቹ ባለፉት 22 ዓመታት በከርሰ ምድር የውኃ ማጠራቀሚያ ላይ የታዩ ለውጦችን ለመመርመር ከአራት የናሳ ሳተላይቶች የተገኙ መረጃዎችን ተጠቅመዋል።

ሳተላይቶቹ የተዘጋጁት የምድርን የውኃ እንቅስቃሴ ለመከታተል ሲሆን፣ በፕላኔቷ ግግር በረዶዎች እና የከርሰ ምድር የውኃ ማጠራቀሚያዎች ላይ የሚመጡ ለውጦችን ሲመዘግቡ ቆይተዋል።

ተመራማሪዎቹም ከሳተላይቶቹ በሚያገኙት መረጃ ላይ ተመስርተው በሠሩት ትንተና  ከአውሮፓውያኑ 2014 የምድራችን ውኃ መጠን በእጅጉ እየቀነሰ ድርቅ በፍጥነት እየተስፋፋ እንደሚገኝ አረጋገጥዋል።

እነዚህ በድርቅ የሚመቱ አካባቢዎች በየዓመቱ ከካሊፎርኒያ ግዛት (423 ሺህ 970 ስኩዌር ኪሎ ሜትር) በእጥፍ በሚበልጥ መጠን እየጨመረ እንደሆነ ፕሮፌሰር ፋሚግሊቲ ተናግረዋል።

ለዚህ እንደምሳሌ ከተጠቀሱት አካባቢዎች አንዱ በመካከለኛው አሜሪካ፣ በሜክሲኮ፣ በካሊፎርኒያ፣ በደቡብ ምዕራብ አሜሪካ፣ በታችኛው የኮሎራዶ ወንዝ እና በደቡባዊው አሜሪካ ከፍተኛ ቦታዎች ይገኛሉ።

በናሳ የጄት ፕሮፐሊሽን ላቦራቶሪ የምድር ሳይንስ ክፍል ሳይንቲስት የሆኑት ቤንጃሚን ሃምሊንግተን በበኩላቸው በምድር ላይ እና ውቅያኖሶች ላይ ለሚከሰተው ለውጥ ምክንያቱ የከርሰ ምድር ውኃ ላይ የሚመጣው ለውጥ እንደሆነ አረጋግጠዋል።

2002 ወዲህ ከግሪንላንድ እና ከአንታርክቲካ በስተቀር እያንዳንዱ ሰፊ መሬት በፍጥነት እየደረቀ እንደሚገኝም ነው ጥናቱ ያረጋገጠው።

ይህ አህጉራዊ ድርቅ በረጅም ጊዜ በሰዎች ላይ ከባድ መዘዝ ያስከትላል ተብሎ ከፍተኛ ስጋት እየፈጠረ ይገኛል።

ሶስት አራተኛ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ የሚኖረው ጨዋማ ያልሆነ የውኃ ሃብት እየተሟጠጠባቸው ባሉ አካባቢዎች መሆኑንም ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባሕሩ እየጨመረ መሄዱ በዓለም ዙሪያ ባሉ የባሕር ዳርቻዎች የሚኖሩት ሰዎችን አደጋ ውስጥ እያስገባ ከመሆኑም በላይ በከባድ አውሎ ነፋስ እና ጎርፍ የሚከሰተው ጫና እንዲባባስ እያደረገ ይገኛል።

በአሜሪካ በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት የባሕር ዳርቻዎች በሚገኙ ከተሞች ላይ የሚፈጠረው ውድመት የኢንሹራንስ ቀውስ እንዲከሰት እያደረገ እንደሚገኝ መረጃዎቹ አመላክተዋል።

በአጠቃላይ በባህር ወለል መጨመር እና የከርሰ ምድር ውኃ አየተመናመነ መሄድ መካከል ያለው ግንኙነት ለፕላኔቷ የውኃ ዑደት መዛባት ምክንያት እየሆነ ይገኛል ነው የጥናቱ ድምዳሜ፡፡

በሳንታ ባርባራ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የምድር ሳይንስ ዲፓርትመንት ፕሮፌሰር የሆኑት አሌክሳንደር ሲምምስ እንደገለጹት የከርሰ ምድር ውኃን በማዛባት የሚመጣው ለውጥ ቋሚ ወይም ቢያንስ ለሺህ ወይም ለአስር ሺህ ዓመታት ሊስተካከል የማይችል ነው።

ጥናቱ በማጠቃለያው በዚህ ጉዳይ ላይ ሁሉም ግንዛቤ ኖሮት በፍጥነት እርምጃ ካልተወሰደ ምድራችን ወደማትወጣው ፈተና ውስጥ ትገባለች፤ ድርቅ፣ ረሃብ እና ቸነፈር የፕላኔቷን ህልውና ይፈታተኗታል የሚል ነው፡፡

 

በለሚ ታደሰ