ነገን በማሰብ ዛሬን በትጋት

2 Days Ago 303
ነገን በማሰብ ዛሬን በትጋት

ዓለም በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈች ነው። ጦርነት እና ወንጀል፣ የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እሽቅድድም እና የኢኮኖሚ ቅኝ ግዛት እርምጃዎች፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖ እና የተፈጥሮ ቁጣ እንዲሁም የተለያዩ ወረርሸኞች እና ሰው ሠራሽ ችግሮች የዓለም ሀገራትን በተለይም የአዳጊ ሀገራትን ሕዝብ እየፈተኑ ከሚገኙት ችግሮች መካከል ከብዙዎቹ በጥቂቱ ናቸው።

በዚህ ውስብስብ ችግሮች በበዙባት ዓለም እንደሀገር ጠንክሮ ለመውጣት የዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገን ማሰብ ደግሞ ችላ የሚባል ጉዳይ አለመሆኑ በርካቶች ይስማሙበታል።

ልክ አንድ አርሶ አደር ላቡን አንጠፍጥፎ ካመረተው ቀጣዩን ጊዜ ምርት እያሰበ ምርጥ ዘሩን ጠብቆ እንደሚያቆይ ሁሉ ሀገርም እንዲሁ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ ጥሪት ለማቆየት ጠንካራ ሥራን ማከናወን ይጠበቅባታል።

ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ምን ሠራች? ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ አሊያም ልምድ ሆኖ የሚዘልቅ ምን ሥራስ እያከናወነች ነው?

“ኢትዮጵያ ነገን በማሰብ ዛሬን በትጋት እየሠራች መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩትን በቅርቡ ሲጎበኙ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

በተለይ በስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ዘርፍ ነገን ታሳቢ ያደረገ ሥራ በማከናወን በኢንስቲትዩቱ በኩል ከከርሰ ምድር እስከ ስፔስ ድረስ ለልማት የሚያስፈልጉ መረጃዎችን እያጠናቀረች መሆኑንም አንሥተዋል።

የከርሰ ምድር የውኃ ሃብት ያለባቸውን አካባቢዎች እና የኢትዮጵያ ሐይቆች ያሉበትን ሁኔታ የማጥናት እና የውኃ ሃብቶችን የመለየት ሥራ እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በውኃ እና በመሬት ልማት ጥናት እና መረጃ አያያዝ ተስፋ ሰጪ ዕውቀት እየተገነባ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሁለት ሳተላይቶችን ወደሕዋ ያመጠቀችው ኢትዮጵያ ሦስተኛውን ሳተላይት ለማምጠቅ እየሠራች መሆናንም አስታውቃለች።

ይህም “ጣሊያኖች በዚህ አካባቢ ማዕድን እንዳለ አጥንተዋል፤ አሜሪካኖች በዛኛው አካባቢ የነዳጅ ሀብት መኖሩን አጥንተዋል” ከሚል መላምት በመውጣት በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሠረተ የልማት ጥያቄ ለማንሣት እና ለነገ የሚተርፉ ሥራዎችን ለማከናወን የሚረዳ መረጃ ለማጠናቀር እንደሚረዳ እሙን ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ በሳይበር ደኅንነት እና በሮቦት ቴክኖሎጂ ተስፋ ሰጪ ምርምሮችን እያደረገች መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይመሰክራሉ።

በዘርፉ ክህሎት ያላቸውን ተስፈኛ ወጣቶች ለማብቃትም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሰመር ካምፕ ፕሮግራሞችን እና ልዩ ማዕከላት በማቋቋም ይበል የሚያሰኝ ሥራ እያከናወነች መሆኑ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አንዱ ማሳያ ነው።

ከዚህ ባለፈ በችግሮች ውስጥም ቢሆን ኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት፣ በግብርናው፣ በማዕድን እና በተለያዩ ዘርፎች ለነገ የሚተርፍ በርካታ ውጤቶች ማስመዝገቧን የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።

የአፍሪካውያን ኩራት

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነገን አስበው ከሚሠሩ ተቋማት መካከል አንዱ ነው። አየር መንገዱ በኤሌክትሪክ የሚሠራ የአየር ላይ ታክሲ ትራንስፖርት ለመጀመር የሚያስችል ስምምነት ከውጭ ሀገር ኩባንያ ጋር መፈራረሙ አይዘነጋም።

አየር መንገዱ አቅሙን በማጎልበት መዳረሻዎቹን በየጊዜው ከማስፋት ባለፈ ገቢውንም እያሳደገ ነው። በ9 ወራት ውስጥ 5.6 ቢዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አየር መንገዱ አስታውቆም ነበር።

በ9 ወራት አየር መንገዱ 14.5 ሚሊዮን መንገደኞችን በማጓጓዝ የአፍሪካውያን ኩራት መሆኑንም አስመስክሯል።

በየዓመቱ እየጨመረ የመጣውን የመንገደኞች ቁጥር በበቂ ሁኔታ ለማስተናገድም በቢሾፍቱ አቅራቢያ የሚገነባ “ሜጋ ኤርፖርት ከተማ" ፕሮጀክትን ይፋ አድርጓል።

በ5 ቢሊዮን ፓውንድ የሚገነባው ፕሮጀክቱ በ2029 ሲጠናቀቅ እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን በዓመት የሚያስተናግድ ትልቅ ተርሚናል እና አራት ማኮብኮቢያዎችን ይይዛል ተብሏል። 

ይህም ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ንግድ እና ቱሪዝም ዋና ተዋናይ ለማድረግ ያለመ መሆኑን አየር መንገዱ አመላክቷል።

ኢኮኖሚ

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልከው ይልቅ ወደ ሀገር የምታስገባቸው ምርቶች እንደሚልቁ የየዓመቱ የወጪ እና ገቢ ምርቶች መረጃ አመላካች ነው።

ይህን ለመቀየር ደግሞ የሀገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ እና የኢኮኖሚ አካሄዱን መቀየር አስፈላጊ መሆኑ አጠያያቂ አይሆንም።

በዚህ ረገድ ከሦስት ዓመታት በፊት በተጀምረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪው አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን አምራቾች ጭምር ተናግረውታል።

የኢንዱስትሪዎችንም የማምረት አቅም ከ46 በመቶ በሦስት ዓመት ተኩል ውስጥ ወደ 61 በመቶ በማሳደግ ረገድ ውጤት መመዝገቡን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በተጨማሪ የዘመናዊ ሕትመት ኢንዱስትሪዎችን፣ የቴክኖሎጂ እና የፕላስቲክ እንዲሁም የመድኃኒት ማምረቻ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን ከመገንባት ባለፈ ያሉትም በማነቃቃት እና አሠራራቸውን በማደስ ረገድ ሠፊ ሥራ መከናወኑን መመልከት ተችሏል።

በማዕድኑ መስክ

በማዕድን ዘርፍ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ወደ ምርት ማስገባት የተቻለ ሲሆን፣ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ የወርቅ እና የድንጋይ ከሰል ፕሮጀክቶች ተጠቃሾች ናቸው።

የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ የኢትኖ ማይኒንግ፣ የአኮቦ ሚኒራልስ ኩባንያ፣ በፖታሽ እና በተለያዩ ማዕድን ምርት ላይ ተመርኩዘው የተከፈቱ ፋብሪካዎች ገቢ ከመጨመር ባለፈ ለሥራ ዕድልም እየፈጠሩ ነው። 

ከነችግሮቹም ቢሆን የወርቅ ምርትም ገቢ አያደገ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። ባለፉት 9 ወራት ውስጥ 26 ቶን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ቀርቦ ከ2.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት መቻሉም ተገልጿል።

በግብርና ምርታማነት

ኢትዮጵያ የጠንካራ አርሶ አደሮች ሀገር ብትሆንም የልፋታቸውን እና የመሬቱን ለምነት ያክል ግን በቂ ምርት ይገኛል ማለት አይቻልም።

ይህን ለመቀየርም ሜካናይዜሽንን በማስፋፋት እና ምርጥ ተሞክሮዎችን በመተግበር ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ይገልጻል።

በተከናወኑ ሥራዎችም በዚህ ዓመት 7.9 ሚሊዮን ሔክታር የሚሆን መሬት በስንዴ መሸፈኑን እና ከዚህም ከ300 ሚሊዮን ኩንታል ያላነሰ ምርት ይስበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመልክተዋል።

ይህም በግብርና ምርት የአነስተኛ አርሶ አደሮች የሰብል ሽፋን 20.5 ሚሊዮን ሔክታር እንዲደርስ ማድረጉን መረጃዎች ያሳያሉ።

በተመሳሳይ ቡና እና ሻይ ምርትም ውጤት ተገኝቷል። ቡና በለውጡ ዋዜማ 700 ሚሊዮን ገደማ በዓመት ኤክስፖርት ይደረግ ነበር፤ ዘንድሮ ግን በ10 ወራት ብቻ ከቡና ወጪ ንግድ ሪከርድ የሰበረ 1.87 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገልጿል።

በየዘርፉ ለሚመዘገበው የግብርና ምርት ደግሞ በየዓመቱ የሚተከሉ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኞች የራሳቸው በጎ አስተዋፅኦ እንዳላቸው የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎችም ይስማሙበታል።

የባህር በር አማራጮች

ጂቡቲ ወደብ ላይ የተመሠረተውን የወጪ እና ገቢ ምርት ለማሳለጥ ተጨማሪ ወደቦችን ማማተር እንደሚያስፈልግ ኢኮኖሚስቶች ያነሣሉ።

በዚህ ረገድ ከላሙ ወደብ ተጠቃሚነት ባለፈ ከሶማሊያ እና ሶማሊ ላንድ ጋር የተደረሱ ስምምነቶች ተጠቃሽ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባሕር በር ጥያቄ ሌሎች ሀገራት የደገፉት እና በጋራ ተጠቃሚነት ሊሳካ የሚችል ፍትሐዊ ጥያቄ መሆኑን የመሠከሩለት ነው ሲሉ መደመጣቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ ነገን የማሰብ ውጤት መሆኑን እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበር በሰላማዊ መንገድ ሊተገበር የሚገባው መሆኑንም የፖለቲካ ምሁራን የሚያነሡት ጉዳይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም “ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ጉዳይ ከቀጠናው ሀገራት ጋር በሰላም መተባበር የምትፈልግ እና ትንኮሳ የማትሰነዝር ሀገር መሆኗን ላረጋግጥ እወዳለሁ” ሲሉም መናገራቸው ይታወሳል።

የሕዳሴ ግድብ

የአፍሪካውያን የይቻላል መንፈስ ማሳያ የሆነው የሕዳሴው ግድብ ወደማጠናቀቂያው ምዕራፍ ደርሷል።

ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት ባለፈ አሁን ላይ የዓሣ ምርት እያስገኘ ነው፤ ከዚህም በተጨማሪ ለውኃ ላይ ትራንስፖርት እና ለቱሪዝም መስህብነት ዐምቅ አቅም እንዳለው በዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ጭምር ከወዲሁ ተመስክሮለታል።

ግድቡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም ለግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ጎልህ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል። ለዚህም ስኬት መላው ዜጋ የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ግድቡን በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ በጋራ ሪቫን በመቁረጥ ታሪክ እናደርገዋለን” ሲሉ ከሳምንታት በፊት ለፓርላማ ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም።

ግድቡ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጭምር ፋይዳው የጎላ መሆኑን አሁን በተግባር ለማየት እንደተቻለም ከዚህ ቀደም አንሥተዋል።

እነዚህን እና ሌሎች ለነገው ትውልድ የሚተርፉ ሥራዎችን በማከናወን ረገድ አያሌ ሥራዎች ቢሠሩም ያልተሻገርናቸው ችግሮች መኖራቸውም ደግሞ በበርካቶች ይገለጻል።

በተለይ የሰላም ጉዳይ ሰፊ ጥረትን የሚጠይቅ እና የጋራ መግባባትን የሚሻ ጉዳይ መሆኑ ይነሣል።

ሀገር አቀፍ ፕሮጀክቶችን ቀጣይ ለማድረግ እና የሕዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰላም አስፈላጊ ከሆኑ ጉዳዮች ዋነኛው ነው።

በየአካባቢው ጥያቄ ያላቸው አካላት በሰላማዊ መንገድ ችግሮቻቸውን መፍታት እንደሚገባቸው አብዛኛው ኅብረተሰብ ይስማማበታል።

በዚህ ረገድ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚረዳው የሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ እየተከናወነ ይገኛል።

ለነገ የተሻለች ሰላማዊ ሀገር እንዲኖረን ሀገራዊ ምክክሩ አስፈላጊ በመሆኑ ደግሞ ደሀውም፣ ሀብታሙም፣ አክቲቪስቱም ወጣቶችም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም፣ የሃይማኖት አባቶችም በጥቅሉ መላው ዜጋ በንቃት ሊሳተፉበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑ አያጠያይቅም። ቸር እንሰንብት!

በጌትነት ተስፋማርያም 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top