በልጅነቷ ለራሷ የገባችውን ቃል ያሳካችው የብዙዎች እናት

2 Days Ago 761
በልጅነቷ ለራሷ የገባችውን ቃል ያሳካችው የብዙዎች እናት

ከ40 ዓመታት በፊት ነው። የ9 ዓመቷ የሶስተኛ ክፍል ተማሪ ዘመናይ አስፋው ከዕድሜ እኩዮቿ ጋር ወደ ትምህት ቤት በመሄድ ላይ ሳሉ አንድ ትኩረታቸውን የሚስብ ነገር ይመለከታሉ።

ነገሩ እንዲህ ነው። በትልቁ የሰፈሩ የቆሻሻ ገንዳ ዙሪያ በቁጥር የበዙ አሞራዎችና ውሾች ያንዣብባሉ ይንከላወሳሉ።

ውሾቹ  በቡድን ሲጠጉ አሞራዎቹ ይበራሉ፤ በተቃራኒው ደግሞ አሞራዎቹ በመንጋ ገንዳው ላይ ሲያርፉ ውሾቹ ይሸሻሉ።

በዚህ ትዕይንት ትኩረታቸው የተወሰደው ሕፃናቱ ወደ ገንዳው ሲጠጉ ያልገመቱትን ተመለከቱ።

የጠዋቱ ብርድ ያንሰፈሰፍው ከተጣለበት የቆሻሻ ገንዳ የሚያነሳው፤ አቅፎ ሙቀት የሚሰጠው ቤተሰብ የሚሆነውን በጉጉት የሚጠባበቅ ጨቅላ ህፃን ይመለከታሉ።

በሁኔታው የተደናግጡት ህፃናቱ እሪታቸውን አቀለጡት።

ይህን የሰሙት የአካባቢው ነዋሪዎች ገንዳውን ከበቡት። ዘመናይ እና ጓደኞቿ ደግሞ የትምህርት ቤት መግቢያ ሰዓት ስለረፈደባቸው የተሰበሰቡት ሰዎች ለህፃኑ መፍትሄ ይሰጣሉ ብለው አስበው ከስፍራው ይሄዳሉ።

ሆኖም ዘመናይ ወደ ቤቷ የምትመለስበት ሰዓት እስኪደርስ ድረስ ጠዋት ያየችው ህፃን እንዴት እንደሆነ እያሰበች መዋሏን አትዘነጋውም።

ሰዓቱ ደርሶ ከትምህርት ቤቷ ስትወጣ ግን ነገሩ እንዳሰበችው አልሆነም። 

ሰዎች ከገንዳው አንስተውት ቤተሰብ ያገኛል ያለችው እምቦቀቅላ  በሕይወት ትተውት ሄደው እዛው እገንዳው ስር ሞቶ፣ ተቀብሮ ተመለከተች።

"የዛኔ ከ40 ዓመት በፊት በልጅነት ልቦናዬ ነበር ሳድግ እንዲህ የተጣሉ ልጆችን አንስቼ አሳድጋለሁ፤ ወላጅ አፈላልግላቸዋለሁ ብዬ ለራሴ ቃል የገባሁት" ትላለች ዘመናይ።

የጅማ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ዘመናይ አስፋው ከተለያዩ የሕይወት ውጣ ውረዶች በኋላ በልጅነቷ የገባችውን ቃል የምታሳካበትን አጋጣሚ ፈጠረች።

በ2010 ዓ.ም ሰው ለሰው የተሰኘ የበ አድራጎት ድርጅት በማቋቋም ወላጅ አልባ ሕጻናትን ማሳደጓን ተያያዘችው።

መጀመሪያ ስላነሳችው ልጅ ስትገልጽ፥ "ዮሐንስ ይባላል። እናቱን በሞት ያጣ አባቱ ደግሞ በቀን ስራ የሚተዳደር ስለነበር፤ ወደ ስራ ሲሄድ ለአራስ ልጁ ዮሐንስ በጡጦው አጥሚት ሞልቶ ሰጥቶት ይሄዳል" ትላለች።

ብቻውን ባዶ ቤት ያለተንከባካቢ የሚውለው ህጻን በተኛበት የሳር ፍራሽ ላይ ሲንቀሳቀስ  አጥሚት የተሞላው ጡጦ ወደ ጆሮው መፍሰስ ይጀምራል።

ይህ አደጋ በተደጋጋሚ በመከሰቱ ለጆሮ ሕመም ይዳረጋል።

በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ዮሐንስ እጅግ ተጎድቶ እና ታምሞ ስለነበር ይሞትብሻል አትውሰጂው እየተባልኩ በልጅነቴ የገባሁትን ቃል ኪዳን አስታውሼ አቅፌ ወደ ቤቴ አስገባሁት ትላለች።

"ከሶስት ወራት በኋላ አትውሰጂው ይሞታል ላሉኝ ሰዎች ሳሳያቸው እጅግ ተደነቁ፤ እኔም  ደስ አለኝ። ይህን ለዩሐንስ የሰጠሁትን ዕድል ለሌሎችም መስጠት እንዳለብኝ አስቤ ወደ ስራ ገባሁ" ስትል ትገልጻለች።

ዘመናይ ከ10 ዓመታት በፊት በዮሐንስ የተጀመረውን ይህን መልካም ተግባር በማስፋት 149 ሕፃናትን ከፖሊስ እንዲሁም ከጅማ ከተማ ሴቶች እና ህፃናት ቢሮ ተቀብላ እያሳደገች ትገኛለች።

ለ78 ህፃናት አሳዳጊ አፈላልጋ ቤተሰብ እንዲያገኙ ማድረጓንም ታስረዳለች።

ይህ ብቻ ሳይሆን ጧሪ ያጡ አዛውንቶችን እንዲሁም የአዕምሮ ጤና እክል ያለባቸውን እና ረዳት የሌላቸውን ሰዎች በበጎ አድራጎት ድርጅቷ አስጠልላ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገችላቸው ትገኛለች።

በራሄል አብደላ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top