እኛ ወንድማማቾች እንጂ ጠላቶች ስላልሆንን በጠላትነት ከመፈራረጅ ወጥተን ችግሮቻችንን በንግግር በመፍታት ሀገራችንን በጋራ መገንባት አለብን ሲሉ ብ/ጄኔራል ዋሲሁን ንጋቱ ተናገሩ።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለፈዴራል ተቋማት እና ማኅበራት ባዘጋጀው የምክክር መድረክ የተሳተፉት ብ/ጄኑራል ዋሲሁን ንጋቱ፥ በመድረኩ በርካታ ጉዳዮች ስለተነሱ የተነሱ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ለመፍታት እና የጋራ ሃሳብ ላይ ለመድረስ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ሁሉንም የሚወክሉ ሀሳቦች እንዲነሱ የኮሚሽኑ ሠራተኞች ሁሉጊዜም የሚያደርጉት ጠንካራ ዝግጅት እና ትጋታቸው የሚደነቅ መሆኑንም ብ/ጄኔራል ዋሲሁን ንጋቱ ገልጸዋል።
ጦርነት ከውድመት እና ሀገርን የኋሊት ከመጎተት ውጭ ችግሮችን እንደማይፈታ ኢትዮጵያ በታሪኳ ስላየች፤ አሁን ቁጭ ብለን መነጋገርና ችግሮቻችንን ለመፍታት የሰለጠነ መንገድን መከተል ምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ለዚህም መንግሥት የከፈተውን የሰላም በር በማጽናት በጫካ ያሉ ወገኖች ወደ ሰላም እንዲመጡ መደረግ አለበት ብለዋል።
በተለያዩ ቦታዎች ሆነው ከመንግሥት ጋር ወደ ግጭት የገቡ አካላትም ቢሆኑ ከሰላም የበለጠ አማራጭ ስለሌለ ወደ ሰላም በመምጣት ለሀገር ግንባታ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው ያሉት ብ/ጄኔራል ዋሲሁን፤ ለዚህ ደግሞ የምክክር መድረኩ ሊያመልጥ የማይገባ ዕድል እንደሆነ ተናግረዋል።
የውጭ ወራሪ እንጂ ቅሬታ ያለባቸው የሀገር ልጆች ጠላቶች መባባል የለባቸውም ያሉት ብ/ጄኔራል ዋሲሁን ንጋቱ፤ መንግሥት እንደ ከውጭ መንግሥታት ጋር እንኳን የሚያደርጋቸው ስምምነቶች ለሰላም ያለውን ፍላጎት ማሳያ ስለሆነ ይህን ዕድል መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።
30 ዓመታትን በጦር ሠራዊት ውስጥ መቆየታቸውን ያውሱት ጄኔራል መኮንኑ፣ በዚህ ቆይታቸው የታዘቡት ነገር በጦርነት ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኝ ችግር እንደሌለ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ እንኳን ለራሷ ሌላውን የምታስታርቅ ለመሆኗ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳንን፤ እንዲሁም የናይጄሪያን መንግሥት እና ተገንጣይ የነበረውን ባያፍራን አደራድራ ውጤታማ መሆኗ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን ዓይነት የችግር መፍቻ መንገድ ለራሳችንም መጠቀም አለብን ብለዋል።
በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተጀመረው መሰረት ያሉንን ቅሬታዎች ወደ ጠረጴዛ አምጥተን በውይይት በመፍታት ወንድማማችነታችንን ማጽናት አለብንም ብለዋል።
በለሚ ታደሰ