የቻይና የኢንዱስትሪ እና ንግድ ባንክ የአሜሪካ ቅርንጫፍ በመረጃ ጠላፊዎች ጥቃት ደረሰበት

8 Mons Ago
የቻይና የኢንዱስትሪ እና ንግድ ባንክ የአሜሪካ ቅርንጫፍ በመረጃ ጠላፊዎች ጥቃት ደረሰበት

በተቀማጭ ሀብት መጠን የዓለማችን ትልቁ ባንክ የሆነው የቻይናው የኢንዱስትሪ እና ንግድ ባንክ /The Industrial and Commercial Bank of China (ICBC)/ የአሜሪካ ቅርንጫፍ በመረጃ ጠላፊዎች ጥቃት እንደ ደረሰበት ተገልጿል። 

ባንኩ በደረሰበት የራንሰምዌር ጥቃት ከአሜሪካ ግምጃ ቤት ጋር የነበረው የንግድ ልውውጥ ተስተጓጉሎ እንደነበር ተነግሯል።

በቻይና የኢንዱስትሪ እና ንግድ ባንክ ላይ የደረሰው ይህ የሳይበር ጥቃት በዚህ ዓመት በቤዛ ጠያቂ ጠላፊዎች ከደረሱት በርካታ የሳይበር ጥቃቶች የቅርብ ጊዜው ነው ተብሏል።

የባንኩ የአሜሪካ ቅርንጫፍ ፋይናንስ ክፍል ባወጣው መግለጫ፣ “አንዳንድ ሥርዓቶችን ያወከው” ሲል የገለጸውን ጥቃት እየመረመረ እና ከጥቃቱ ለማገገም የማሻሻል ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ገልጿል። ጥቃቱ ከፍተኛ ጉዳት እንዳላደረሰ እና በቁጥጥር መዋሉንም ነው ያስታወቀው። 

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ዓርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ አበዳሪ ባንኩ ከጥቃቱ በኋላ ያለውን አደጋ እና ኪሳራ ለመቀነስ እየጣረ ነው ብሏል።

በICBC ዋና መሥሪያ ቤት፣ በዓለም ዙሪያ ባሉ ሌሎች ቅርንጫፎች እና ደጋፊ ተቋማት ያሉ የንግድ ሂደቶች በመደበኛነት እንደሚቀጥሉ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የብሪታኒያ የፋይናንስ ሥነ-ምግባር ባለሥልጣን ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ባወጣው መግለጫ፣ “በዩናይትድ ኪንግደም የፋይናንስ አገልግሎቶች ላይ የሚደርሱትን ተፅዕኖዎች ለመለየት ከሚመለከታቸው የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ባለሥልጣናት እና ኩባንያዎች ጋር እየተነጋገርን ነው" ብሏል።

መረጃ ጠላፊዎች (ሐከሮች) እንደዚህ ዓይነት ጥቃቶችን ሲፈፅሙ የተጎጂውን ድርጅት ሥርዓት ይቆልፋሉ፤ የድርጅቱን ሥርዓት መልሶ ለመክፈትም ቤዛ ይጠይቃሉ።

በርካታ የራንሰምዌር ባለሙያዎች እና ተንታኞች እንዳሉት ‘ሎክቢት’ /LockBit/ የተባለ አደገኛ የሳይበር ወንጀል ቡድን በICBC ላይ ከደረሰው ጠለፋ ጀርባ እንዳለ ይታመናል፤ ‘ሎክቢት’ም ተግባሩን መፈፀሙን ዓርብ ዕለት ማረጋገጡ ተገልጿል።

እንደ ሲቢሲ ኒውስ ዘገባ ‘ሎክቢት’ የተባለው ዲጂታል የወንበዴዎች ቡድን በካናዳ እና በሌሎች ሀገራት ከፍተኛ የሆነ የራንሰምዌር ስጋት ተብሎ የተሰየመ ነው።

ፎርቹን የተባለ የዜና ምንጭ በበኩሉ፣ "ጥቃቱን ያደረሰው የሩሲያ የመረጃ ጠላፊ ቡድን ሊሆን እንደሚችል ይጠረጠራል" ብሏል።

የሩሲያው አር.ቲ ደግሞ በጉዳዩ ላይ ባወጣው አጠር ያለ ዘገባ፣ “የቻይናው ትልቁ ባንክ በደረሰበት የሳይበር ጥቃት መረጃ ለመለዋወጥ ዩኤስቢ (በተለምዶ ፍላሽ) የምንለውን ለመጠቀም ተገድዷል” ብሏል።

‘ሪከርድድ ፊውቸር’ በተባለ የሳይበር ደኅንነት ተቋም ባለሙያ የሆኑት አለን ሊስካ፣ በቻይናው የኢንዱስትሪ እና ንግድ ባንክ ላይ የደረሰው ዓይነት የራንሰምዌር ጥቃት ብዙውን ጊዜ ሲፈፀም እንደማይታይ ገልጸው፣ የአሁኑ ጥቃት የራንሰምዌር ጥቃት አድራሾች ቡድን ድፍረት እየጨመረ የመምጣት አዝማሚያን ይጠቁማል ብለዋል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኩባንያዎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ የሳይበር ወንጀሎችን በተለይም የራንሰምዌር ጥቃቶችን መግታት እንዳልቻሉ የዜና ምንጩ ጠቁሟል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top