ከኢትዮጵያ እና ከእውነት ጎን የቆሙ ታሪካዊ ዐርበኞች

3 Days Ago 402
ከኢትዮጵያ እና ከእውነት ጎን የቆሙ ታሪካዊ ዐርበኞች

ማንኛውም ዜጋ ለተወለደባት እና ለሚኖርባት ብቸኛ ሀገሩ ዋጋ መክፈሉ ምንም የሚያጠያይቅ አይደለም። ምክንያቱም ሀገር መተኪያ የሌላት ነችና።

ዋጋውም በነፃነት መኖር እና ለትውልድ ነፃ ሀገር ማውረስ እንዲሁም ለዘላለም መታሰብ ነው።

ለዚህም ይመስላል ዐርበኛም ዲፕሎማትም የነበሩት ሐዲስ ዓለማየሁ በአንድ ወቅት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ "ዐርበኛም ዲፕሎማትም ሆነህ ሀገርህን አገልግለህ እንዴት ርስት አልኖረህም?" ብለው ለጠየቋቸው ጥያቄ፣ "ዐርበኛ ብሆን ለራሴ ነፃነት ነው፤ ዲፕሎማት ብሆን በሀገሬ ለመክበር ነው፤ ታዲያ ለራሴ ብዬ ለሠራሁት ሥራ እንዴት ከሀገሬ ዋጋ እጠይቃለሁ?" ብለው የመለሱላቸው።

‘መወለድ ቋንቋ ነው!’ የሚል የኢትዮጵያውያን አባባል አለ። ይህ አባባል በአንድ በኩል በሥጋ የተዛመደ ሰው ምንም ቢመጣ የማይለያይ እና የቁርጥ ቀን ከመጣም ለተወለዱት የሚሞት መሆኑን የሚያሳይ ነው።

ከዚህ በተቃራኒ ግን ሳይወለዱ በሆነ አጋጣሚ ተገናኝተው ከተወለዱት በላይ ማንኛውንም ዋጋ የሚከፍሉ ሰዎችን ሲገኙ ነው ‘መወለድ ቋንቋ ነው!’ የሚባለው።

የዛሬውን የዐርበኞች ቀንን በማስመልከት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ይህን አባባል አውን ያደረጉ ሁለት ባለውለታዎችን እንመለከታለን።

እነዚ ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ አልተወለዱም፤ ኢትዮጵያንም አያውቁአትም ነበር፣ ነገር ግን ግፍ ሲደርስባት ለፍትሕ ብለው ከጎኗ ቆሙ።

የዛሬው ባለ ታሪኮቻችን እነ ማን ናቸው?

ሲልቪያ ፓንክረስት

ሲልቪያ ፓንከረስት በትውልድ እንግሊዛዊት ቢሆኑም በተጨባጭ ተግባራቸው ግን የኢትዮጵያ ዐርበኛ ነበሩ። ልጃቸው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እና የልጅ ልጃቸው አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) ሌላው የእርሳቸው ቤተሰብ ለኢትዮጵያ ያበረከታቸው ስጦታዎች ናቸው። ለዚህ ታሪካቸውም ዋቢ የሚሆነን የልጃቸው ሪቻርድ ፓንክረስት “Sylvia Pankhurst, Counsel for Ethiopia” መጽሐፍ ነው።

ሲልቪያ ፓንክረስት የተወለዱት እ.አ.አ ሜይ 5 ቀን 1882 በኦልድትራፎርድ ስቴትፎርድ ዩናይትድ ኪንግደም ነበር።

20 ዓመት ሲሆናቸውም የሞዛይክ (mosaic) ሥነ ጥበብ ለማጥናት እ.አ.አ በ1902 ቬኒስ ከተማ እንዲሁም በ1919 ለጉብኝት ቦሎኛ ከተማ በሄዱባቸው ወቅቶች የሞሶሎኒን ፈሺስትነት ተረድተዋል።

ኢትዮጵያን ለመውረር ዝግጅቷን ያጠናቀቀችው ጣሊያን ኅዳር 26 ቀን 1927 ወልወል ላይ ግጭት ስትጀምር ቀድመው ተቃውመዋል።

የሙሶሊኒ ዓላማ ኢትዮጵያን በሙሉ ለመውረር መሆኑን በመገንዘብም በወቅቱ ለነበረው የመንግሥታት ማኅበር (League of Nations) ብዙ የአቤቱታ ደብዳቤዎች ጽፈው ጠይቀዋል።

የትውልድ ሀገራቸው እ.አ.አ በ1935 በሰር ጆን ማፊ የተመራ ኮሚቲ አቋቁማ ጥናት አስጠንታ ጣሊያን ኢትዮጵያን ብትወርር እንግሊዝን የሚጠቅማት እንጂ የሚጎዳት አለመሆኑን መጠቆሟ የበለጠ አስገረማቸው። እነዚህ ጫናዎችም እስከ ሕይወታቸው ፍፃሜ ድረስ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ አደረጉአቸው።

ጣሊያን በዓለም ላይ የተከለከለውን ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ ፈጽማ “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል” እንደሚባለው መልሳ ኢትዮጵያን ትከስስ ነበር።

ኢትዮጵያ የደረሰባትን ግፍ ያክል ድምፅ የሚያሰማላት አልነበራትም፤ ሲልቪያ ፓንክረስት ግን ለኢትዮጵያ ድምጽ ሆኑላት።

በዚህም እንደ ቢቢሲ፣ ዴይሊ አክስፕሬስ፣ ማንቸስተር ጋርዲያን፣ ዴይሊ ቴሌግራፍ፣ ኒውካስትል ክሮኒክል እና ሌሎች መገናኛ ብዙኃን ላይ የኢትዮጵያን ድምፅ አሰምተዋል።

“የአውሮፓ ሕሊና ሞቷል ወይ? በእንግሊዝ ሀገር ታማኝ አስተሳስብ ጠፋ ወይ?” እያሉ ነበር ስለኢትዮጵያ ጉዳይ የአውሮፓን ሕዝቦች ስሜት ለመቀስቀስ ሲሞክሩ የነበሩት።

"ኢትዮጵያ በባሪያ ንግድ ትጠቀማለች" በማለት ፋሺሽቶች ያሰራጩ የነበረውን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ አጋልጠዋል።

በፀረ ፋሺሽት እና ፀረ ኮሎኒያሊስት መርሆ ተሠማርተው የነበሩትን እነ ጆሞ ኬንያታን፣ ኤሚ አሽውድን፣ ጋርቬይን እንዲሁም የሙሶሊኒ ተቃዋሚ የነበሩ ጣሊያናውያንን ጭምር በኢትዮጵያ ጉዳይ አስተባብረዋል።

በወቅቱ በለንደን ከነበሩት ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ (ቻርለስ ማርቲን) ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ እና ሱዳን ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር በመጻጻፍ ወቅታዊ መረጃዎችን ያገኙ ነበር።

ጣሊያንን ለመታገል ወደ ሱዳን ወጥተው የነበሩት ኢንጂነር አያና ብሩም አንደኛው የመረጃ ምንጫው ነበሩ።

ለዓለም መንግሥታት ማኅበር፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርቺል፣ ለእንግሊዙ ሊቀጳጳስ፣ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሩዝቬልት እና ለሌሎችም ኃያላን የአቤቱታ ደብዳቤዎችን ጽፈዋል።

እ.አ.አ በ1936 “New Times and Ethiopia News” የተሰኘ ጋዜጣ አቋቁመው ስለኢትዮጵያ ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ግንዛቤ እንዲዳብር አድርገዋል። የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም የአዲስ አበባን ጭፍጨፋ አጋልጠዋል።

በ1933 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከፋሺሽት ነፃ ከወጣች በኋላ ኢትዮጵያ በእንግሊእ ቁጥጥር ስር (protectorate) እንድትቆይ በእንግሊዝ ጦር መሪዎች የተቀነባበረውን ሴራ በማጋለጥም እንዲከሽፍ በማድረግም ግንባር ቀደም ናቸው።

በዚህ ተግባራቸውም እንደ ኮሎኔል ጊልበርት ማክበረት የነበሩ ቁልፍ የእንግሊዝ ባለሥልጣናት ስለ ሲልቪያ የሚሰማቸውን ቁጣ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የተሟላ ነፃነቷን ስትጎናጸፍም በአጼ ኃይለሥላሴ በተደረገላቸው ጥሪ ወደ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው በመምጣት ቀሪ ሕይወታቸውን ለኢትዮጵያ ኖረዋል።

ካርል ጉዝታቭ ቮን ሮዘን

አርክቴክት እና ደራሲ ሚካኤል ሽፈራው “An Air Borne Knight Errant” የተሰኘ የእግሊዝኛ መጽሐፍ፣ “ከማይጨው እስከ ኦጋዴን” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ መልሰዋል።

የዚህ መጽሐፍ ባለታሪክ ኢትዮጵያ ውጥረቶች ውስጥ በገባችባቸው ዘመናት በቅንነት እና በፍቅር ያገለገሏት ባለውለታዋ ናቸው።

እኒህ ግለሰብ በዜግነታቸው ስዊድናዊ ቢሆንም ለኢትዮጵያ ለመሠዋት ግን አላመነቱም። ራሳቸውን ለከፍተኛ አደጋ አጋልጠው ኢትዮጵያን በሙሉ ልብ እና በቆራጥነት አገልግለዋል።

በ1928 ጣሊያን ኢትዮጵያን መውረሯ በስዊድን በተሰማ ጊዜ ከፍተኛ ቁጣ ተቀሰቀሰ። ጋዜጦቿም የጣሊያንን ወረራ በብርቱ አወገዙ። ጦርነቱ ከተጀመረበት ዕለት አንሥቶ የስዊድን ቀይ መስቀል ኮሚቴ ስዊድናውያን የሕክምና ባለሞያዎችን ያካተተ የጦር ሜዳ ሆስፒታል ልኮ ለኢትዮጵያውን ደርሷል።

በጊዜው የ26 ዓመት ወጣት አብራሪ የነበሩት ካርል ጉስታቭ ቮን ሮዘን ኢትዮጵያ ላይ ስለተከፈተው የጣሊያን የግፍ ጥቃት የሚተርከው ንግግር ዶክተር ጉናር በተባሉ ሐኪም ሲደረግ ከሰሙ በኋላ የአምቡላንስ አውሮፕላን እብራሪ ሆነው ወደ ኢትዮጵያ ለመዝመት ወሰኑ።

የግል አውሮፕላናቸውንም ለቀይ መስቀል አገልግሎት እንድትውል በስጦታ አበረከቱ።

ካርል ኢትዮጵያ ሲደርሱ በጊዜው በጦርነቱ የነበሩት ኢትዮጵያዊ ካፒቴን ሚሽካ ባቢ ሼፍ እና ሉድዊግ ዌበር የሚባል በአንደኛ የዓለም ጦርነት የተዋጋ አውሮፕላን አብራሪዎች ብቻ ነበሩ።

ካርል ከንጉሡ በቀጥታ የተለያዩ ትዕዛዞችን በመቀበል በመሣሪያ እና በመርዝ ጋዝ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ሲያነሡ እና ሲረዱ ቆይተዋል።

ይዘዋት የመጡት አውሮፕላን በኢትዮጵያ ተራራማ ሥፍራዎች እና አየር ንብረት ምክንያት የማታገለግል ስትሆንም ባገኙት መጓጓዣ ጉዳት ወደ ደረሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ በመጓዝ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ አድርገዋል።

ጣሊያን የስዊድን የጦር ሜዳ ሆስፒታልን በቦምብ በደበደበ ጊዜ ካርል ግዳጃቸውን እየተወጡ ሳለ ከሞት ለጥቂት ተርፈዋል።

ጣሊያን ተሸንፋ ወጥታ ንጉሡ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱም ካርል ጉዝታቭ በአምስቱ ዓመት ውጊያ ኢትዮጵያ የተበለጠችበትን የአየር ውጊያ ክፍተት የሚሸፍን ሥራ ሠርተዋል።

ከስዊድን አየር ኃይል ጋር በመወያየት አጥጋቢ አገልግሎት መስጠት የሚችል የአየር ኃይል በአጭር ጊዜ ውስጥ አቋቁመዋል። ዛሬ የኢትዮጵያን ሰማይ ያስከበረው የኢትዮጵያ አየር ኃይል የአርሳቸው አሻራ ያለበት ነው።

ኢትዮጵያ ስትገፋ የማያስችላቸው ካርል የዚያድ ባሬ ጦር ኢትዮጵያን ሲወርር የሚችሉትን ድጋፍ ለማድረግ ተመለሱ።

በዚያ ጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን ሲረዱም ቆዩ። በአንድ ክፉ ቀን ግን የዚያድ ባሬ ጦር እርሳቸው ባሉበት አካባቢ ድንገተኛ አደጋ ጣለ።

እርሳቸውም በዚያ ያልተጠበቀ አደጋ ለኢትዮጵያ ሰማዕት ሆነው ወደ ዘላለማዊ እረፍት ሄዱ።

እነዚህ ሁለቱ ባለውለታዎች ከኢትዮጵያ እና ከእውነት ጎን በመቆማቸው ታሪክ ሲዘክራቸው ይኖራል።

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top