የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስት ድርጅት (ኢጋድ) ዓመታዊ የሚኒስትሮች ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የኢጋድ ዋና ዳይሬክተር ተወካይ እና የድርጅቱ የጤናና የልማት ዳይሬክተር ፈትያ አልዋን፤ ቀጠናው የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች፣ የዜጎች መፈናቀል እና ስደት በስፋት የሚስተዋልበት መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣናው በሀገር ውስጥ ፍልሰት ከ19 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች መኖራቸው እና ከ 5 ሚሊዮን በላይ ደግሞ ከሀገራቸው ውጭ በቀጠናው ሀገራት በስደተኞች መጠለያ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
ለስደተኞች ዘላቂ መፍትሄን ለመስጠት እ.ኤ.አ በ2016 አባል ሀገራቱ የተስማሙበት የናይሮቢ ድንጋጌ አፈፃፀም መርሃ ግብር የተገመገመ ሲሆን፤ በተፈለገው ደረጃ ባይሆንም ኢትዮጵያን ጨምሮ የኢጋድ አባል ሀገራት የተሻለ አፈፃፀም ሂደት ውስጥ መሆናቸው ተነስቷል።
ለስደተኞች ህይወት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የኢጋድ አባል ሀገራት በትብብር እና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያ፣ ጁቡቲ እና ሌሎቹ ሀገራትም ለስደተኞች መፍትሄ የሚሰጡ ጉዳዮችን በፓሊሲያቸው ማካተት የቻሉ ናቸው ተብሏል።
በቀጠናው የስደተኞችን ህይወት በዘላቂነት መፍትሄ ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት የሚሻ ጉዳይ ስለመሆኑም ተገልጿል።
በሰለሞን አበጋዝ