የሐሞት ጠጠር በሐሞት ከረጢት ውስጥ በሚገኝ የሐሞት ፈሳሽ አልያም ሐሞትን ከጉበት ወደ አንጀት በሚወስዱት ቱቦዎች ውስጥ የሚፈጠር ባዕድ ነገር ነው።
የሐሞት ፈሳሽ በጉበት ሕዋሳት የሚመረት፣ ጨዋማ ንጥረ ነገሮችን ያዘለ ሲሆን የምንመገባቸው ቅባት እና ቫይታሚኖች እንዲፈጩ ይረዳል። በሰውነታችን የሚገኙ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን ለማጥፋትም ይጠቅማል።
የሐሞት ጠጠር መንሥኤዎች
80 በመቶ የሚሆነው የሐሞት ጠጠር የሚከሰተው በቅባት አልያም በኮሌስትሮል መብዛት መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የሐሞት ጠጠር ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ነገሮች ደግሞ፡-
• ቅባታማ ምግቦችን ማዘውተር
• ከልክ ያለፈ ውፍረት
• በሰውነት ያለ ቅባት ለመቀነስ የሚረዱ መድኃኒቶችን መውሰድ
• በነፍሰ ጡርነት ጊዜ ከልክ ያለፈ ውፍረት
• የወሊድ መቆጣጠሪያ ክኒን
• የዕድሜ መግፋት በተለይ (በሴቶች ላይ በሽታው ይዘወተራል)
• ስኳር ሕመምና እና የመሳሰሉት ናቸው።
የሐሞት ጠጠር በሽታ ምልክቶች
የሐሞት ጠጠር ለረዥም ጊዜ የሕመም ስሜትን ሳያሳይ ሊቆይ ይችላል። ሐሞት የሚወጣበት ቱቦ በሐሞት ጠጠር በሚዘጋበት ጊዜ በቀኝ የሆዳችን የላይኛው ክፍል ላይ እየመጣ የሚመለስ ወይም የማያቋርጥ የሕመም ስሜትን ያስከትላል።
የሐሞት ጠጠር በሽታ ወደ ጨጓራ እንዲሁም ወደ ቀኝ ትከሻ እና ጀርባ የመሠራጨት ባሕሪም አለው። የሕመም ስሜቱ የቅባት እህል ከተመገብን በኋላ መባባስ ከጨጓራ ሕመም እንደንለየው ይረዳል።
ዋና ዋና ምልክቶቹ፡-
• ቅባት ነክ ምግቦችን ስንመገብ ያለመስማማት
• ከምግብ በኋላ የሚፈጠር የመጠዝጠዝ ስሜት
• የማቅለሽለሽ እና የማስመለስ ችግር
• ማስገሳት
• የምግብ ፍላጎት መቀነስ
• በሰውነት ላይ ቀያይ ነጠብጣብ መኖር
• በእንቅልፍ ሰዓት የሕመም ስሜት መታየት
• ዐይን ቢጫ መሆን
• የሰውነት ቆዳ ወደ አረንጓዴ ቢጫነት መቀየር
• የዐይን፣ የቆዳ እና የሽንት ቀለም ቢጫ መሆን
• የሰገራ ቀለም መቀየር
• በቀኝ ጎናችን በላይኛው ክፍል አካባቢ እጅግ ከባድ የሆነ ሕመም
የሐሞት ጠጠር መከላከያ መንገድ
• የተመጣጠነ ምግብ መመገብ
• የምግብ ሰዓታትን ሳይመገቡ አለማሳለፍ
• በቂ ውኃ መጠጣት
• የሰውነትን ክብደት በፍጥነት ያለመቀነስ ጥቂቶቹ ናቸው
የሐሞት ጠጠር በሽታ ሕክምና
የበሽታው የሕመም ስሜት ከፍተኛ ከሆነ የቅባት ምግቦችን መመገብ ማቆም እና የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን መውሰድ ለጊዜው ሕመሙን ያስታግሳል።
በርግጥ አንድ ሰው ምልክቶቹ ስለታዩበት ብቻ መድኃኒት ከመውሰዱ በፊት የሐሞት ጠጠር እንዳለበት በምርመራ ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው።
ሕመሙ እየበረታ ከሄደ ግን የሐሞት ጠጠሩን በቀዶ ሕክምና ማውጣት እንደሚገባ የሕክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ቀዶ ጥገና ማድረግ የማይቻል ከሆነ ደግሞ ለበሽታው ተገቢውን መድኃኒት በመጠቀም ጠጠሮቹን ማሟሟት ይቻላል፤ ይኽኛው መንገድ ግን ብዙ ዓመታትን እንደሚፈጅ የህክምና ሳይንስ መረጃዎች ያመለክታሉ።