በማዕድን ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለኃብቶች አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር ገለፀ

8 Mons Ago
በማዕድን ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለኃብቶች አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር ገለፀ

ከማዕድን ኃብት ያላትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አገራዊ የማዕድን ካውንስል ተቋቁሞ እየተሰራ እንደሚገኝ የማዕድን ሚንስትር ኢንጂነር ኃብታሙ ተገኝ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) 2ኛውን ዓመታዊ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ትላንት በሚሊኒየም አዳራሽ መርቀው ከፍተዋል።

ኤክስፖው ዛሬም የቀጠለ ሲሆን የማዕድን ሚንስቴር ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የማዕድን ኃብትና በዘርፉ የሚከናወኑ ኢንቨስትመንት ተግባራትን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

የማዕድን ሚንስትሩ ኢንጂነር ኃብታሙ ተገኝ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት አገሪቱ በርካታ የተፈጥሮ ማዕድን ኃብት ያላት ብትሆንም ይህንን ኃብት አልምቶ በመጠቀም ብዙ ርቀት አለመጓዟን አንስተዋል።

ዘርፉ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት መሰረት የሚጥል ቢሆንም በቀደሙት ጊዜያት ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱን ገልጸዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ኃብት መለየትና ኃብቱን ማስተዳደር የሚያስችል አቅም በመገንባት በኩል ውስንነቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ነገር ግን ከለውጡ ማግስት ጀምሮ መንግስት የብዝሃ ኢኮኖሚ አተያይን ተግባራዊ በማድረጉ የማዕድን ዘርፍ አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶ ተደርጎ መወሰዱን ተናግረዋል።

መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት ከአገሪቱ የማዕድን ኃብት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የማዕድን ዘርፍ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚፈልግ በመሆኑ ምሁራንን ጨምሮ የዘርፉ ባለድርሻዎች ድጋፍ ወሳኝ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የማዕድን ኃብትን ጥቅም ላይ ለማዋል ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚጠይቅና ረጅም ጊዜ የሚፈልግ መሆኑም በዘርፉ እድገት ላይ የራሱን ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ጠቁመዋል።

ለዚህም ባለኃብቶች አቅማቸውን በማሰባሰብ በዘርፉ በኢንቨስትመንት በጋራ የሚሰማሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩም በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለኃብቶች አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በመጠቆም።

ኢትዮጵያ ከማዕድን ኃብት ያላትን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲቻል አገራዊ የማዕድን ካውንስል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የጂኦሎጂ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ታረቀኝ ታደሰ በበኩላቸው ከማዕድን ዘርፍ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ የማዕድን ኃብት ባለቤት እንደሆነች ጠቁመው ይህን ኃብት ለመጠቀም በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይልን መጠቀም፣ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋትና ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ፈሰስ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትላንት በሚሊኒየም አዳራሽ የተከፈተው የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ እስከ ህዳር 18/2016 ዓ.ም ይቆያል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top