"በበጎ ደም ለጋሾች የቤተሰባችን ደስታ በመቀጠሉ እኛም ለሌሎች ደስታ ሳናቋርጥ እንለግሳለን" - እህትማማቾቹ

3 Mons Ago
"በበጎ ደም ለጋሾች የቤተሰባችን ደስታ በመቀጠሉ እኛም ለሌሎች ደስታ ሳናቋርጥ እንለግሳለን" - እህትማማቾቹ

እህትማማቾቹ ጸጋ፣ ሀና እና ሊዲያ ትዕግስቱ ይባላሉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ናቸው።

በበጎነት በሚለግሱት ደም የሌሎች ህይወትን ለመታደግ በየጊዜው ደማቸውን ያለማቋረጥ በመለገስ ላይ ይገኛሉ።

እስከ አሁንም ሀና ትዕግስቱ 26 ጊዜ እንዲሁም ጸጋ እና ሊዲያ ትዕግስቱ እያንዳንዳቸው 17 ጊዜ በሆሳዕና ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ ደማቸውን ለግሰዋል።

እህትማማቾቹ በተከታታይ ደም የሚለግሱበትን ምክንያት ሲጠየቁ ጸጋ የተባለችው ታላቅ እህታቸው በ2007 ዓ.ም ድንገተኛ የመኪና አደጋ ደርሶባት ወደ ህክምና ተቋም ስትወስድ የደም እጥረት ገጥሟት ስለነበር በጎ የሆኑ ሰዎች ከለገሱት 2 ዩኒት ደም ተሰጥቷት ህይወቷ መቀጠል መቻሉን ይናገራሉ።

የፈጣሪ እና የሀኪሞች እርዳታ ተጨምሮበት በጎ ደም ለጋሾች በመኖራቸው እና በጊዜ ደም ማግኘት በመቻሏ እህታችን ዛሬ አብራን በህይወት ልትኖር ችላለች ሲሉም ይገልጻሉ፡፡

እህትማማቾቹ ልደትና ምረቃትን ጨምሮ ልዩ ፕሮግራም ሲኖራቸው ወደ ደም ባንክ በመሄድ እና ደም በመለገስ እንደሚያከብሩ መናገራቸውን ከሀዲያ ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ከመኪና አደጋ የተረፈችው እህታቸው የዩኒቨርስቲ ትምህርቷን ስታጠናቅቅ የምረቃ ስነ-ስርዓቷን በሆሳዕና ደም ባንክ እንዳደረገችም ገልፀዋል።

ከአደጋው የተረፈችው እህታቸው ጸጋ ትዕግስቱ ይህን ለምን እንዳደረገች ስትጠየቅ ደም በሚለግሱ በጎ ፈቃደኞች እርዳታ ህይወቴ ተርፏል፤ ያቺን ቀን ለማሰብና እኔም ለሌሎች ለመድረስ ነው ቀኑን በተለየ መልኩ ደም በመለገስ ያሳለፉኩት ትላለች።

"ደም መለገስ የሚያመጣው ምንም አይነት የጤና ጉዳት የለም እንዳውም ጤነኛና ደስተኛ ያደርጋል። ለዚህም እኛ ህያው ምስክሮች ነን" ሲሉም ይመክራሉ። 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top