የሃገር መከላከያ ሰራዊት ሃገር ለማስቀጠል በሚከፍለው የህይወት ዋጋ የምንጊዜም የሃገር ባለውለታ ነው - አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

1 Mon Ago
የሃገር መከላከያ ሰራዊት ሃገር ለማስቀጠል በሚከፍለው የህይወት ዋጋ የምንጊዜም የሃገር ባለውለታ ነው - አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

መከላከያ ሰራዊታችን የአድዋን አርበኞች ፈለግ በመከተል ህብረ-ብሄራዊ አንድነትን ፈጥሮ ሃገር ለማስቀጠል በሚከፍለው የህይወት ዋጋ የኢትዮጵያ ህዝብ የምንጊዜም ባለውለታ ነው ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል።

አምባሳደሩ ይህን ያሉት 128ኛውን የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በማስመልከት ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር "አድዋን ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሃገረ መንግስት ግንባታ" በሚል መሪ ቃል ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ነው።

በመድረኩ የጅማ ዩንቨርሲቲ ምሁራንና ተማሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የዳሉል ማዕከላዊ ዕዝ ከፍተኛ የሰራዊት አመራሮችና አባላት ጥናታዊ ፅሁፍ አቅራቢዎችና ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ፤ ዘመን አይሽሬ የሆነውን ታላቁን የአድዋ ድል በአል የዘመናችን የሃገር ባለውለታ ከሆኑት የማዕከላዊ ዕዝ የሰራዊት አባላቶች ጋር ስናከብር አድዋ እንደ ታሪክ ያወረሰንን ህብረ-ብሄራዊ አንድነት በማሰብና ከአድዋ የተረከብነውን የአሸናፊነት የፅናትና የጀግንነት መንፈስ በተሰማራንበት የስራ ዘርፍ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል በመግባት መሆን አለበት ብለዋል። 

የማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ዘውዱ በላይ በበኩላቸው እኛ ወታደሮች ከአድዋ ታሪክ ድል አድራጊነትን ተዋግተው ድሉን ካስመዘገቡት ጀግኖች አባቶቻችን በፈተና ሁሉ ፀንቶ የማለፍ ብቃትንና ጀግንነትን በየጊዜው እንማራለን ሲሉ ገልፀዋል።

ሌተናል ጀኔራል ዘውዱ በላይ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ አጥብቀው የሚሹትን ሰላምና ልማት እውን ለማድረግ ምሁራንና ሃገር ተረካቢው ወጣት ሃይል ሰከን ብሎ ማሰብና ነገሮችን በርጋታ መመልከት ይኖርበታል ማለታቸውን ከሃገር መከላከያ ሠራዊት ይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፅ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top