ዪን ዩዜን የተባለች የ57 ዓመቷ ቻይናዊት ሴት በ35 ዓመታት ውስጥ በርሃማውን ቦታ ወደ ገነት መቀየሯ ተሰምቷል።
በቻይና ካሉት አራት ዋና ዋና በረሃዎች አንዱ በሆነው የሙ ኡስ በረሃ ውስጥ ሞንጎሊያ ግዛት በረሃውን ወደ ነፋሻማ ፓርክ በመቀየር አስደናቂ ተግባር የፈፀመች ቻይናዊት እናስተዋውቃችሁ።
ዪን ዩዜን ትባላለች በአውሮፓውያኑ 1965 በጂንግቢያን ካውንቲ የተወለደችው ይህች እንስት ወደ ሙ ኡስ በረሃ ለማቅናት የወሰነችው በትዳሯ ምክንያት ነበር።
ታድያ የሄደችበት ሞንጎሊያ በቻይና ከሚገኙና በጣም ከማይመቹ በረሃማ አካባቢዎች አንዱ ነው።
በጊዜው የ19 ዓመት ልጅ የነበረችው ዩን አባቷ ከዳሯት ባለቤቷ ጋር በመሆን ነበር ወደ ስፍራው ያቀናችው።
ከአሸዋ በቀር ምንም በሌለበት በረሃ ውስጥ በዙሪያዋ ከባለቤቷ በቀር ማንንም ማግኘት ባለመቻሏ ዪን ከአዲሷ ሁኔታዎች ጋር ለመላመድ በጣም ተቸግራ ነበር።
የበረሃው ሕይወት ቢፈትናትም በመጨረሻም ዪን ነገሮችን ወደ እጇ ለመውሰድ ወሰነች።
የራሷን አካባቢ እና በበረሃ የገጠማትን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የበረሃውን ገነት በአካባቢዋ ለመፍጠር ወደ ስራ ገባች።
ታዲያ የዪን ጥረት በጊዜው ስኬታማ አልነበረም።
መጀመሪያ ላይ የቤተሰቧን ከብቶች በመሸጥ በቤቷ ዙሪያ ለመትከል 6 መቶ የዛፍ ችግኞችን ገዛች፣ ነገር ግን ባጋጠማት ከባድ በረሃማ ሁኔታ ከተከለቻቸው ችግኞች የተረፉት አስራ ሁለት ብቻ ነበሩ።
ለዓመታት በባለቤቷ እርዳታ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል በመስራት የተለያዩ የመዝራትና የማብቀል ዘዴዎችን በመሞከር ለሀገር በቀል ዛፍ ዝርያዎች ቅድሚያ በመስጠት የበረሃ ደን የማልማት ስራዋን ቀጠለች።
ዪን በ35 አመታት ውስጥ ከ3 መቶ ሺህ በላይ ሀገር በቀል እፅዋትን እና ዛፎችን በ10 ሺህ ሄክታር በረሃማ መሬት ላይ በመትከል በረሃማነትን በብቃት በማሸነፍ ለእርሻ ተስማሚ የሆነ አረንጓዴ ምድር መፍጠር ችላለች።
የ57 ዓመቷ ዪን ዩዜን የደን ልማት ስራዋ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ እውቅናዎችን አስገኝቶላታል።
በውጤታማነቷና በዚህ ታሪኳ ምክንያት ዪን ከሀገሯ መንግስት እና ከተለያዩ አካላት ከ80 በላይ ሽልማቶችንም ተቀብላለች።
ይህ ብቻ ሳይሆን ሌሎች በበረሃ የሚኖሩ የሀገሪቱ ነዋሪዎች የእሷን እርምጃ እንዲከተሉ አነሳስቷልም።
ዪን ዩዜን በቻይና ውስጥ ካሉት አስር በጣም ተፅኖ ፈጣሪ ሴቶች አንዷ ሆናም ሁለት ጊዜ ተመርጣለች።
በናርዶስ አዳነ