ምክር ቤቱ የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባ ሥርዓት አዋጅን አጸደቀ

1 Mon Ago 336
ምክር ቤቱ የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባ ሥርዓት አዋጅን አጸደቀ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 18ኛ መደበኛ ስብሰባው የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባ ሥርዓት አዋጅን አጽድቋል።
 
ምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባ ሥርዓትን ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አድምጧል።
 
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ነጎ (ዶ/ር)፥ የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባ የመንግስት አገልግሎቶችን ለማቀላጠፍና የዜጎችን የወሳኝ ኩነቶች መረጃ በተደራጀ መልኩ ለመያዝ ያስችላል ብለዋል።
 
በአግባቡና በወቅቱ የተመዘገቡ ወሳኝ ኩነቶችና የቤተሰብ ምዝገባ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የልማት ዕቅዶችን በማሳካት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሚናቸው የላቀ መሆኑንም ጠቁመዋል።
 
ከዚህ አኳያ የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባ አዋጅ ከኢትዮጵያውያን ባለፈ ነዋሪነታቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ የውጭ ሀገር ዜጎች እንዲመዘገቡና የተሻለ የደህንነት ጥበቃ እንዲኖር እንደሚያስችልም ነው ያነሱት።
 
አዋጁ የሚመለከታቸው አካላት በሕግ በሚሰጣቸው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት በቅንጅት እንዲሰሩ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
 
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል በነበረው አዋጅ የሲቪል ምዝገባው በአግባቡና በተደራጀ መልኩ ባለመቀመጡ በጉዞና በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ክፍተት ፈጥሯል ብለዋል።
 
በሌሎች አገሮች የተጠናከረ የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባ በመኖሩ አገልግሎቶችን ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግ ማስቻሉንም ጠቅሰዋል።
 
ልደትና ጋብቻን ጨምሮ ወሳኝ ኩነቶችን በአግባቡ መዝግቦ መያዝ ለሀገር የልማት ፖሊሲ ዝግጅትና ክለሳ ወሳኝ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
አዋጁ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚደረጉ የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባዎች በቴክኖሎጂ ታግዘው በተናበበ መልኩ እንዲሆን አጋዥ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top