የወርዋሪው ሮሪ ዴላፕ ልጅ ሊያም ዴላፕ
ሮሪ ዴላፕ ይባላል፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለደርቢ ካውንቲ፣ ሰንደርላንድ፣ ሳውዝሀምፕተን እና ስቶክ ሲቲ ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ በተለይ ለስቶክ ስቲ በተጫወተባቸው አምስት አመታት በሚጠቀማቸው የመልስ ውርወራዎች ብዙዎች ያውቁታል፡፡
ሀይልን በቀላቀለ አጨዋወቱ የሚታወቀው የአሰልጣኝ ቶኒ ፑሊስ ስብሰብ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ከነበራቸው ተጫዋቾች አንዱ ነበር፡፡ የአየር ላንድ ሪፐብሊኩ አማካይ የቅጣት ምት እና የማእዘን ምት ያክል በሚያስፈሩ ውርወራዎቹ በበርካታ አጋጣሚዎች ክለቡ ውጤት ይዞ እንዲወጣ አድርጓል፡፡
በስቶክ ሲቲ ቆይታው በውርወራ ብቻ 24 ቀጥታ ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶም አቀብሏል፡፡

በ2008/09 የውድድር አመት ስቶክ ሲቲ በሊጉ አርሰናልን 2 ለ 1 ባሸነፈበት ጨዋታ ሮሪ ዴላፕ አመቻችቶ በማቀበል እና በጨዋታው በሚወረውራቸው ኳሶች የነበረው አስፈሪነት አርሰን ቬንገር ጨዋታው እግር ኳስ አይመስልም የሚል ሃሳብ እንዲሰነዝሩም አድርጓቸው ነበር፡፡
አሁን ደግሞ ልጁ ሊያም ዴላፕ የፕሪሚየር ሊጉ ተስፋ የተጣለበት ኮከብ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡ በተያዘው የክረምቱ የተጫዋቾ የዝውወር መስኮት ከኢፕስዊች ታውን ወደ ቼልሲ አምርቷል፡፡
ከእግሩ ይልቅ በእጁ በሚወረውራቸው ኳሶች በተጽዕኖ ፈጣሪነቱ የሚታወቀው ሮሪ ዴላፕ ልጅ በትምህርት ቤት የራግቢ ተጫዋች ነበር፡፡ እንደ አባቱ በእጁ መጫዎት የሚቀናው ሊያም ዴላፕ በልጅነቱ ጎበዝ የራግቢ ተጫዋች እና በአጭር ርቀት ሩጫ የተዋጣለት አትሌት እንደነበር በትምህርት ቤት የስፖርት ሳይንስ መምህሩ የነበሩት ሰው ማርክ ሴለርለማንችስተር ኢቭኒንግ ተናግረዋል፡፡ የእግር ኳስ ህወቱን በደርቢ ካውንቲ አካዳሚ የጀመረው ዴላፕ ለማንችስተር ሲቲ ከ18 አመት በታች ቡድን ከነ ኮል ፓልመር፣ ሞርጋን ሮጀር እና ሮሚዮ ላቪያ ጋር ተጫውቷል፡፡
ለዋናው የሲቲ ቡድንም ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር አመት በኢፕስዊች ታውን በግሉ ድንቅ ጊዜን ያሳለፈው ሊያም ዴላፕ በማንችስተር ሲቲ ቤት የጋርዲዮላ ረዳት የነበሩት ኢንዞ ማሬስካ በተያዘው የዝውወር መስኮት ወደ ቼልሲ ወስደውታል፡፡
ባሳለፈባቸው አካዳሚዎች ፈጣን እና ጨራሻ እንደሆነ የሚነገርለት የ22 አመቱ ዴላፕ በምዕራብ ለንደን አዲሱ 9 ቁጥር ለባሽ ኮከብ ሆኖም ተከስቷል፡፡
በአንተነህ ሲሳይ