አን ካትሪን በርገር ትባላለች ጀርመናዊት ግብ ጠባቂ ናት፡፡ በአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች በፒኤስጂ፣ ቼልሲ እና በርሚንግሀም ለመሳሰሉ ክለቦች ተጫውታለች፡፡ ሀገሯንም ከ2020 ጀምሮ በታላላቅ መድረኮች ወክላለች።
ሕይወት 2ኛ ዕድል ከሰጠቻቸው ሰዎች አንዷናት፡፡ አስቸጋሪ የሚባለው የካንሰር ህመም ከአንድም ሁለት ጊዜ ያቀረበላትን ፈተና በድል ተወጥታለች፡፡
አን ካትሪን በርገር በ2017 የበርሚንግሃም ተጫዋች በነበረችበት ጊዜ ነው ለመጀመርያ ጊዜ የታይሮይድ ካንሰር ህምም እንዳጋጠማት በህክምና ያረጋገጠችው፡፡
በዚሁ ምክንያት ከእግር ኳስ የተገለለችው ግብ ጠባቂዋ ለ4 ወራት ባደረገችው ህክምና ከባድ የሚባለውን ህመም አሸንፋ ዳግም ወደ ሜዳ ተመለሰች፡፡ የበርሚንግሃም ውሏን ስታጠናቅቅ በ2019 ወደ ቼልሲ የተዛወረችው በርገር በምዕራብ ለንደኑ ክለብ እያለች ለ2022ቱ የአውሮፓ ዋንጫ በጀርመን ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ደረሳት፡፡
በእንግሊዝ አስተናጋጅነት በተካሄደው የአውሮፓ ዋንጫ በርገር የስብስቡ አካል ብትሆንም በበርሚንግሀም እያለች ገጥሟት የነበረው የካንሰር ህመም እንደገና ተመለሰባት፡፡
በመድረኩ አንድም ጨዋታ ማድረግ ያልቻለችው ግብ ጠባቂ ለሁለተኛ ጊዜ የገጠማትን ካንሰር በብዙ የህክምና ክትትል እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አሸንፋ ወደ እግር ኳስ ሜዳ ተመልሳለች፡፡
አን ካትሪን በርገር አስቸጋሪውን የካንሰር ፈተና ከተወጣች በኋላ ከቼልሲ ጋር አራት የሱፐር ሊግ ዋንጫዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 10 ክብሮችን በማሸነፍ የተሳኩ አመታትን አሳልፋለች፡፡
ከዚህ ሁሉ ፈተና ያመለጠችው በርገር በሲውዘርላንድ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የሴቶች አውሮፓ ዋንጫ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ቁጥር አንድ ግብ ጠባቂ ሆና እያገለገለች ትገኛል፡፡
34ኛ አመቷ ላይ የምትገኘው ካትሪን በርገር ጀርመን በሩብ ፍጻሜው ፈረንሳይን በመለያ ምት አሸንፋ ለግማሽ ፍጻሜ ስትደረስ ትልቁን የቤት ስራ በብቃት ተወጥታለች፡፡ ገና በ13ኛው ደቂቃ አንድ ተጫዋቿን በቀይ ካርድ ያጣችው ጀርመን ከ75 ደቂቃ በላይ በፈረንሳይ ብትፈተንም ለፈተና አዲስ ባልሆነችው ግብ ጠባቂ የግል ጥረት ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅላለች፡፡
እንደ አቦሸማኔ የምትወረወረው ካትሪን በርገር በጨዋታው 9 ግብ መሆን የሚችሉ ሙከራዎችን እና ሁለት የመለያ ምቶችን አድናለች፡፡
በካንሰርም በፈረንሳይ ግብ አዳኞችም የተፈተነችው በርገር በአውሮፓ ዋንጫ ታሪክ በጥሎ ማለፍ ጨዋታ ያዳነቻቸው ኳሶች ብዛት ከ2013 በኋላ 2ኛው ትልቅ ቁጥር ሆኖም ተመዝግቧል፡፡
ሀገሯን ለግማሽ ፍጻሜ ያበቃችወ የ34 አመቷ ግብ ጠባቂ ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ጀርመን ለፍጻሜ ለማለፍ ከስፔን በምታደርገው ጨዋታ ለሌላ ታሪክ ተዘጋጅታለች።
በአንተነህ ሲሳይ