የፖለቲካ ፓርቲዎች ሠላምን በማስፈንና በማጽናት የሚኖረን ሚና ላይ የቢሾፍቱ ቃል ኪዳን (ዲክላሬሽን)
ሰላምን በማስፈንና በማጽናት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ላይ የሚመክር የሠላም ኮንፍረንስ መድረክ አካሂደናል።
ለመድረኩ በጋራ ም/ቤት ዕቅድ መሠረት የተለያዩ ዝግጅቶች ሲደረጉ የቆየ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ከኢፌዴሪ ሠላም ሚኒስቴር ጋር በመሆን ዕውን ማድረግ ተችሏል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ሠላምን ማስፈንና ማጽናት በሚል መሪ ሃሳብ የሚመክር ሀገራዊ መድረክ በመዘጋጀቱ ምስጋናችን የላቀ ነው።
በመድረኩ ሀገራዊ የሠላም አውድና እና ዓለም አቀፍ ገጽታውን በንድፈ ሃሳብና በተለያዩ ተሞክሮዎች ለሀገራችን ሠላም መስፈንና ማጽናት ባለው ፋይዳ ላይ በምሁራን በቀረቡ የውይይት ሰነዶች ላይ ተመስርተን የሠላምን ምንነትና መገለጫዎችን፣ በሰላም ላይ ቀጠናዊ እና ዓለማዊ ሁኔታ የሚኖረውን ተጽዕኖ እንዴት መቋቋም ይቻላል? የሰላም ተዋኒያን ማንነት እና ሃላፊነት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና እና በመጨረሻም የሀገራችን የሰላም ችግር መነሻዎችና የመፍትሄ አቅጣጫ ላይ በጥልቀት ተወይተናል።
ይህም እንዲሳካ በውይይት ቡድን በመከፋፈል በዝርዝር ከተመለከትን በኋላ በውይይት ነጥቦች ዙሪያ ተቀራራቢ ግንዛቤ ለመያዝ እድል አግኝተናል። በዚህም፡-
• ሠላም የሁሉ ነገር መሠረት መሆኑን፣
• እኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሠላማዊ የፖለቲካ ትግል ተምሳሌት መሆናችንን በመገንዘብ፣
• ለቆምንለት የህብረተሰብ ክፍል፣ ሃገር እና ትውልድ ሰላም እንዲጸና እንደ ፖለቲካዊ መሪዎች ሃላፊነት መወጣት እንዳለብን በማመን፣
• ሠላም ለዲሞክራሲ ስርኣት ግንባታ ያለውን የማይተካ ሚና በመገንዘብ፣
• ይህን እምነታችንን በዚህ የቢሾፍቱ የቃል ኪዳን መግለጫ ይፋ ስናደረግ ለተግባራዊነቱ የባለድርሻ አካላትም ሚናቸውን አንዲወጡ በነዚህ ባለ 7 አንቀጽ የቃል ኪዳን ነጥቦች ጥሪያችንን እናቀርባለን።
አንቀጽ 1: ሠላማዊና የሠለጠነ የፖለቲካ አካሄድ የመከተል ቃል ኪዳን
1.1. የፖለቲካ ዓላማችንን በዲሞክራሲያዊ እና በሕግና በስርዓት እናከናወናለን።
1.2. ጸጥታን በማደፍረስ፣ የስም ማጥፋትና ጥላቻ እንዲሁም ለሰው ህይዎትና ንብርት መጥፋት ምክንያት ባላመሆን ለሰላም እንተጋለን።
አንቀጽ 2: ለዲሞክራሲ ተቋማትና እሴቶች ክብር የመስጠት ቃል ኪዳን
2.1. ሕግና ሥርዓት፣ የህዝብ ውሳኔ ወሳኝነት፣ የምርጫ ሂደቶችና ውጤት እንዲከበሩ።
2.2 በውሳኔዎች ላይ ልዩነት ቢኖር እንኳ ህጋዊነትን በማክበር አቋማችንን ማራመድ።
አንቀጽ 3: ለአካታችነት፣ ለሀገራዊ መግባባትና ብሄራዊ ጥቅም አብሮ የመቆም ኪዳን
3.1. ያሉንን ልዩነቶችን ክብርና ልዩ ትኩረት በመስጠት ለህብረብሄራዊነት እሳቤ ግንባታ ለመስራት ተስማምተናል።
3.2. የወጣቶች፣ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እንድያድግ በትኩረት እንሰራለን።
3.3. ለብሄራዊ ጥቅም አብሮ የመቆም የፖለቲካ ባህል አንገነባለን።
አንቀጽ 4: ለዲሞክራሲያዊ መልካም አስተዳደር መስፈን የመስራት ቃል ኪዳን
4.1. በአጀንዳ፣ በፖሊሲ፣ በችሎታ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት ለመገንባት እንሰራለን።
4.2. የተለያዩ የፖለቲካ አስተሰሰብና ፍላጎት መኖር እንደ ጤናማ ዲሞክራሲ ምልክት እንቀበላለን።
አንቀጽ 5: የግጭት አያያዝ እና የሰላም ግንባታ ውጤታማነት የመስራት ቃል ኪዳን
5.1. በየፓርቲዎቻችን ውስጥና በሌሎች ፓርቲዎች መካከል ለግጭቶች ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮች ላይ የመፍትሄ ሥርዓቶችን እንገነባለን።
5.2. በማህበረሰብ፣ በአካዳሚያ፣ በተለያዩ መድረኮች እና ከፖለቲካ አመራሮች ጋር በሚካሄዱ የሰላም ውይይቶች በአጋርነት እንሳተፋለን።
አንቀጽ 6: የግልጽነትና የተጠያቂነት መርህ የመዳበር ቃል ኪዳን
6.1. በመንግስት እንዲሁም በፓርቲያችን ውስጥ ግልጽነት፣ የሐሳብ ነጻነትና መተማመን እንዲጎለብት እንተጋለን።
6.2. የህዝብ ተሳትፎ የሚገድብ ሥራ እና ተቋማዊነት የሚጎዳ የፖለቲካ አካሄድ በጋራ አንታገላለን።
አንቀጽ 7: ለብሄራዊ ጥቅም እና ለዲሞክራሲ ስርዓት የመጽናት ቃል ኪዳን
7.1. በሰላም፣ በውጫዊ ችግሮች፣ በብሄራዊ ምርጫ እና በመንግሥት ልማት አካል እንደአንድ አካል እንሰራለን።
7.2. በኢትዮጵያ የዜጎችና ህዝቦች ክብር እና በሀገራች የጋራ ዕጣ ፋንታችን ላይ በጋራ በመቆም ለተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት ለማጽናት እንሰራለን።
መደምደሚያ መግለጫ
ይህ የቢሾፍቱ የቃል ኪዳን መግለጫ፣ እኛ እንደፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ከፍተኛ የሰላም መሪነትን፣ ማህበራዊ ሀላፊነትን እና ከሀገራዊ የጋራ ፍላጎትና ጥቅም በመነሳት ለመስራት ካለን የፖለቲካ ቁርጠኝነት ላይ የተመሰረተ ነው። ከዛሬ ጀምሮ ፖለቲካዊ ልዩነታችን አንደተጠበቀ ሆኖ ለአገርና ለህዝቡ ጥቅም ሲባል በሀገራችን ሠላምን ለማስፈንና ለማጽናት በትጋት ለመስራት እንተጋለን።
ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አውድ ውጪ ያላችሁ የፖለቲካ ሃይሎችና የታጠቁ ቡድኖች ልዩነቶችን በሠላማዊ ጠረጴዛ ዙሪያ አንዲፈታ ሚናችሁን አንዲትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ለስኬታማነቱም ሚናችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን።
በሀገራችን ሠላምን ለማስፈንና ለማጽናት የሚያግዙ ስልቶችን ተግባራዊ በማድረግ ከሚመለከታቸውና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበትና በትብብር ለመስራት ተስማምተናል።
ሰላም የሁሉ መሰረት ነው!!!
ሐምሌ 17/2017 ዓ.ም
ቢሾፍቱ