Search

በ7 ዓመታት ውስጥ ገቢውን በ30 እጥፍ ያሳደገው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በቤቶች ፍላጎት እና አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት እና በግንባታው ዘርፍ ያለውን አሠራር እና ቴክኖሎጂ ለማሻሻል ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ነው።

ባለፉት ሰባት ዓመታት ሪፎርም ሲያካሄድ የቆየው ኮርፖሬሽኑ በሂደቱ ገቢውን እያሳደገ መጥቶ በዚህ ዓመት ከፍተኛ የተባለ ገቢ አግኝቷል።

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የኮሙኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ አማኑኤል አያሌው ኮሮፖሬሽኑ ከሰባት ዓመት በፊት በጀመረው ሪፎርም ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ለኢቢሲ ዶትስትሪም አብራርተዋል።

ኮርፖሬሽኑ ቀድሞውንም ቢሆን ግዙፍ ሀብት ይዞ እንደነበረ የሚጠቅሱት አቶ አማኑኤል፣ ከሪፎርሙ በፊት በነበረው ሂደት ግን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በተሟላ ሁኔታ ሲወጣ እንዳልነበር እና ገቢውም ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከ2010 ዓ.ም ለውጥ በኋላ በጀመረው ሪፎርም ቀድሞ ከነበረው ቤቶችን ማስተዳደር በተጨማሪ የቤት ልማት ኃላፊነትን ወስዶ ወደ ሥራ መግባቱንም ጠቁመዋል።

ያሉትን ቤቶች በማደስ እና የኪራይ ገቢ በማሻሻል፣ እንዲሁም ሌሎች የገቢ ማስገኛ ዘዴዎችን በመፍጠር ቀድሞ ከኪራይ ብቻ ይሰበስብ የነበረውን ገቢውንም በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጉንም ጠቅሰዋል።

ከኪራይ ይገኝ ከነበረው ገቢ በተጨማሪም በኮንስትራክሽን ግብአቶች አቅርቦት፣ የመንግሥት ተቋማትን በማደስ፣ በተቋራጭነት እና በአማካሪነት የገቢ መሠረቱን እያሰፋ መምጣቱን ገልጸዋል።

እነዚህ የተጠቀሱት የኮርፖሬሽኑን ገቢ የሚጨምሩ ብቻ ሳይሆኑ ወጪውን የሚቀንሱ እንደሆነ አቶ አማኑኤል ጠቅሰዋል።

በዚህም ቀድሞ ለግንባታ ግብአቶች እና ለግንባታ ሲያወጣ የነበረውን ወጪ ቀንሶ በራሱ አቅም ግንባታ መጀመሩ ገቢውን ከማሻሻሉም በተጨማሪ ለጥራትም ሆነ ለፍጥነት አስተዋፅኦ ማድጉን ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ በሪፎርሙ እነዚህን የአሠራር ለውጦች በመዘርጋት እና በመተግባር በዚህ ዓመት 9.34 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የኮሙኒኬሽን ኃላፊው አቶ አማኑኤል ገልጸዋል።

ይህም ከሰባት ዓመት በፊት ከነበረው የ300 ሚሊዮን ብር ገቢ በ30 እጥፍ ያደገ እንደሆነ ነው የጠቀሱት።

ኮርፖሬሽኑ በድሬደዋ እና አዲስ አበባ ከ20 ሺህ ቤቶች በላይ የሚያስተዳድር መሆኑን ገልጸው፣ በቅርቡ የሚጠናቀቁ ቤቶች ወደ ሥራ ሲገቡ ቁጥሩ ከዚህም ከፍ እንደሚል ጠቁመዋል።

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን መንግሥት የግንባታ ዘርፉን ለማሳደግ ያለውን ዓለማ ለማሳካት ዘርፉ ያለበትን የቴክኖሎጂ፣ የፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር በመለወጥ አሻራውን ለማኖር እየሠራ እንደሚገኝ ኃላፊው ጠቅሰዋል።

የዘርፉ ተዋናዮች በሆኑት ደንበኞች፣ ገንቢዎች እና አማረካሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት ከመገፋፋት ይልቅ ወደ ትብብር አድጎ ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን እንደሚሠራም ገልጸዋል።

ኮርፖሬሽኑ ባደረገው ውጤታማ የሆነ ተቋማዊ ለውጥ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ እና ጥራት በማጠናቀቅ ልምድ የሚወሰድበት ተቋም መሆኑንም ጠቁመዋል።

ጥራት እና ፍጥነትን የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ረገድም ግንባር ቀደም እንደሆነ እና በቅርቡም ጥራት እና ፍጥነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ እንደ 3D ያሉ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት እየሠራ እንሚገኝም ተናግረዋል።

በተመጣጠነ ዋጋ፣ በጥራት እና በፍጥነት ፕሮጀክቶችን ገንብቶ በማጠናቀቅ ለደንበኞቹ እያስረከበ ያለው የፌዴራል ቤቶች ኮሮፖሬሽን፣ በግንባታው ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣ መድረሱንም አቶ አማኑኤል ተናግረዋል።

በለሚ ታደሰ እና መሐመድ ፊጣሞ

#EBC #ebcdotstream #FHC #construction #housing