በአዲስ አበባ ከተማ ለተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭ ከሆኑ 348 ስፍራዎች መካከል 247ቱ ቦታዎች ለጎርፍ እና ጎርፍ ለነክ አደጋዎች ተጋላጭ መሆናቸው ተለይቷል።
ከባድ ዝናብ በሚጥልበት ወቅት ጎርፍ፣ የመሬት መደርመስ እና የመሬት መንሸራተት ይከሰታል።
ምንም እንኳን ጎርፍ ተፈጥሯዊ አደጋ እና በተለያዩ ያደጉ አገራትም የሚከሰት ቢሆን ክረምት በመጣ ቁጥር ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች በሚኖሩ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ስጋት ሲፈጠር ይስተዋላል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢ/ር ወንድሙ ሴታ እንደሚሉት፤ በከተማዋ ለንብረት ውድመት እና ለሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነውን የጎርፍ አደጋ ለመቀነስ በተለያዩ ቦታዎች 64 የጎርፍ መከላከያ ግንቦች ተሰርተዋል።
ሰሞኑን የጣለው ከባድ ዝናብ ያስከተው ጎርፍ በከተማዋ በተለይም በጊዮን ሆቴል፣ በአያት ሆስፒታል እና በዓለሞ ባንክ አካባቢ በነበሩ እንቅስቃሴዎች ላይ እክል ፈጥሮ እንደነበር ኢንጂነሩ አስታውሰዋል።
በጊዮን ሆቴል አካባቢ በወንዝ ዳር ልማት ምክንያት ለስትራክቸር ሥራዎች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በጊዜያዊነት የተሰራውን አማራጭ ግድብ ያለፈው የዝናብ ውሃ ተፈጥሯዊ ፍሰቱን በመቀየሩ ምክንያት ወደመንገድና ወደተለያዩ አካባቢዎች መግባቱን አንስተዋል።
በአያት ሆስፕታል አካካቢ ደግሞ ነባር የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሩ በአካባቢው በነበረው ግንባታ ምክንያት የጎርፍ መፋሰሻዎች በኮንስትራክሽን ተረፈ ምርት እና ደረቅ ቆሻሻ ምክንያት በመዘጋታቸው የተጠራቀመው የዝናብ ውሃ በመተኛቱ በተሽከርካሪዎች እና በእግረኞች እንቅስቃሴ ላይ እክል ፈጥሮ እንደነበረም ነው የገለጹት።
የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር በወሰደው አፋጠኝ እርምጃ የውሃ ሙላቱ በሰው ላይ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር እንደተቸለም ነው ኢንጂነሩ ያስታወቁት።
በከተማዋ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አከባቢዎች የሚኖሩ 4 ሺ 600 ሰዎች ተጋላጭነታውን የመቀነስ ፤730 ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ስለሆኑ ወደ ሌሎች ቦታዎች የማዛወር ሥራ መሰራቱንም ነው የተናገሩት።
ጎርፍ በአየር ንብረት ለውጥ አማከኝነት የሚከሰት የተፈጥሮ አደጋ መሆኑን የተናገሩት እንጂነሩ፤ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ቦታዎችን በመለየት ጉዳት እንዳያደርሱ በመከላከል የሕዝብን ደህንነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል ።
በአዲስ አበባ ከተማ የፍሳሽ መሰረተ ልማት ደህንነትን ለመጠበቅ የወጡ ሕጎችን በማያከብሩ አካላት ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወስድ ተገልጿል።
በላሉ ኢታና