2ኛው የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ኢትዮጵያ በምግብ ሥርዓት የሰራቻቸውን ሥራዎች ለዓለም የምታስተዋውቅበት መድረክ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሐኑ ፀጋዬ ተናገሩ።
ከነገ ጀምሮ ለ3 ቀናት ኢትዮጵያ የምታስተናግደው 2ተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ፤ እንግዶችን ለመቀበል አጠቃላይ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
አክለውም በጉባኤው ላይ ከ 4ሺህ 700 በላይ ተሳታፊዎች ይገኙበታል ተብሎ እንደሚገመት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በምግብ ሥርዓት ከማምረት እስከ ምገባ ድረስ ሰፋፊ ሥራዎችን አከናውናለች ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ይህንን የምግብ ሥርዓት ጉባኤ በማዘጋጀቷ የሄደችበትን ርቀት እና ልምዷን ለዓለም ለማሳያት እንደሚጠቅም አንስተዋል።
“ጉባኤው በጎ ተሞክሮዎችን ለአፍሪካም እና ለሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት የምናሳይበት፤ እንዲሁም ኢትዮጵያ የምታመርታቸውን ምርቶች ከሀገር ውስጥ ፍጆታነት በዘለለ ለሌሎች ሀገራት ለመሸጥ የገበያ ትስስር የሚፈጠርበት ነው” ብለዋል።
በምግብ ሥርዓት በኩል በኢትዮጵያ ውስጥ የተሰሩ ሰፋፊ ሥራዎችን በመድረኩ ላይ እንዲሁም ከመድረኩም ውጪ፤ በጉብኝት ለዓለም አቀፍ መንግስታት እና ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የማስተዋወቅ ሥራዎች እንደሚከናወኑም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩት።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ