የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር 2ኛውን የዓለም የምግብ ሥርዐት ጉባኤ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፥
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየሠራን የዓለም የምግብ ሥርዐት ጉባኤን ለማስተናገድ ተዘጋጀተናል!
ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በጀመረቻቸዉ ጥረቶች በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል፤ ለላቀ ስኬትም ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
በዚህ ወሳኝ ወቅት ኢትዮጵያ ከጣልያን መንግሥት እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋርበመቀናጀት 2ኛዉን የዓለም የምግብ ሥርዐት ጉባኤ እንድታዘጋጅ ተመርጣለች።
ይህም በኹለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ግንኙነቶች ውስጥ ኢትዮጵያ እየተጫወተች ያለዉን ሚና የሚጎላ፣ በሥርዐተ ምግብ ዙሪያ የጀመረቻቸዉን ስኬታማ ተግባራት የሚያበረታታ ነው።
ከዐራት ዓመታት በፊት በመጀመሪያዉ የዓለም የምግብ ሥርዐት ጉባኤ ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎች ኢትዮጵያ በምታስተናግደዉ መድረክ ይገመገማል፤ ቀጣይ አቅጣጫዎችም ይቀመጣሉ።
ኢትዮጵያ በምታስተናግደዉ ጉባኤ ርኃብን ስለማስወገድ እና ምግብ ዋስትና፣ ስለአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶች ምክከር ይደረጋል፤ ቀጣይ መወሰድ የሚገባቸዉ ርምጃዎችም ይመላከታሉ።
ኢትዮጵያ ጉባኤዉን የምታስተናግደዉ ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን በማስመዝገብ የማንሰራራት ጉዞን በጀመረችበት ወቅት ነው። ለጉባኤዉ በተሞክሮነት የምታካፍላቸዉ በርካታ ስኬቶችም አላት።
በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በለማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ ስኬታማ ድሎችን አስመዝግባለች። በአየር ንብረት ለውጥ ረገድም ባለፉት በጣት የሚቆጠሩ ዓመታት ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ለዓለም አብነት ናት። ጉባኤዉ በሚካሄድበት በዚህ ክረምትም 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል እየተጋች ነው።
የሚተከሉት ችግኞች የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከማስቻላቸውም በላይ የምግብ ዋስትናን እና ሥርዐተ ምግብን ለማሻሻል ሚና ያላቸው ናቸው።
የዓለም የምግብ ሥርዐት ጉባኤን እንድታስተናግድ ለኢትዮጵያ ዕድል መሰጠቱም ይህንን ጅምር ዕውቅና የሚሰጥ ነው።
ኢትዮጵያ ባለብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ እየገነባች እና ኹለንተናዊ ስኬት እያስመዘገበች ባለችበት በዚህ ወቅት ከሐምሌ 20-22/2017 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ሥርዐት ጉባኤን በአዲስ አበባ ታስተናግዳለች።
በጉባኤዉ የአገር መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ሳይንቲስቶች፣ የምግብ አምራቾች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ የሴቶች ድርጅቶች፣ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ይሳተፋሉ።
ኢትዮጵያም የመዲናዋን ገጽታ በእጅጉ ለውጣ እንግዶችን በላቀ ዝግጅት ለመቀበል ተሰናድታለች። በርካታ ስኬቶቿንም በልምድነት ለማካፈል ተዘጋጅታለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ለዘመናት ያስቀጠሉትን ለኹለትዮሽና ባለብዝኃ ወገን ግንኙነት ትኩረት የመስጠት ልምድ ተጠቅመዉ ጉባኤዉን በላቀ ስኬት ለማስተናገድ በቂ ቅድመ ዝግጅት አድርገዋል።
የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት