የሀገር ሉዐላዊነት ከሚከበርባቸው ጉዳዮች አንዱ በምግብ ራስን መቻል ሲሆን ይህም ነፃነት ያለው ሀገር የሚያስብል አንደኛው መንገድ ነው።
ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ በማስገባት ከሰሃራ በታች ከሚገኙ ሀገራት መካከል ስሟ ይነሳ እንደነበር የግብርና ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪና የኢትዮጵያ ስርዓተ ምግብ ሽግግር ኒውትሪሽን ዋና አስተባባሪ ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር ) ተናግረዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያ በዓመት ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጭ በማድረግ ስንዴን ከውጭ ሀገራት ታስገባ እንደነበር አስተባባሪው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ይህን ታሪክ ለማድረግ እና የምግብ ሉዐላዊነትን ለማረጋገጥ ከተሰሩ ስራዎች መካከል አንዱ የስንዴ ምርታማት ዋናው መሆኑ ጠቁመዋል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ስንዴ ከውጭ ባለማስገባት ቀድሞ የነበራትን መጥፎ ታሪክ ከመቀየር ባለፈ ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ መሆን መቻሏን ነው የተናገሩት።
ከዚህ ባለፍም በሌማት ትሩፋት ከአንድ ዓመት ወዲህ አያት ዶሮዎችን (ግራንድ ፓረንት) የሚባሉ የዶሮ ዝርያዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሀገር በማስገባት የዶሮ እርባታ እንዲስፋፋ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
በሀገር ውስጥ ምርትን እና ምርታማትን ለማሳደግ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ገበሬዎች በተስማሙበት የተለያዩ የእርሻ መሳሪያዎች ተሟልተውላቸው እየሰሩ መሆኑን ደግሞ በኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ሽግግር እና የጤናማ ምግብ አስተባባሪ አንቢሳ ሙለታ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሀገር በቀል ሪፎርሞችን ተግባራዊ በማድረግ ባስመዘገበቻቸው ለውጦች ሁለተኛውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባዔ እንድታስተናግድ መመረጧ ይታወቃል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ