2ኛው የተባበሩት መንግስታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ በኢትዮጵያ በተለያዩ መርሐ ግብሮች በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል።
የኢትዮጵያ እና ጣሊያን መንግስታት በጋራ ባዘጋጁት በዚህ ጉባኤ ላይ፤ የምግብ ሥርዓት ለውጥ ፈጣሪ ወጣቶችን ለማበረታት ያለመ መድረክም ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንም ከጣሊያን ራዲዮ እና ቴሌቪዥን (RAI) ጋር በመተባበር፤ ይህን የለውጥ ፈጣሪ ወጣቶች ምክክር መድረክ በመምራት እና ለዓለም ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ ለተመድ እና ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ምንጭ መሆን ችሏል።
ጉባኤው በዛሬው መርሐ ግብሩ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ተሳታፊዎች በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየሰራችባቸው የሚገኙ ዘርፎችንም ተመልክተዋል።
በጉባኤው ለመሳተፍ የተገኙ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮችና የሀገራት ተወካዮች በምስራቅ ሽዋ ዞን የቦራ የስንዴ ክላስተር ማሳን ጎብኝተዋል።
በአዳማከተማ እየተከናወነ ያለውን የዶሮ እርባታና የወተት ልማት ክላስተርም በዛሬው ዕለት ከጎበኟቸው መካከል ይጠቀሳል።
ከዚህ ባለፈ የጉባኤው አካል የሆነ እና የአፍሪካን የቡና እሴት ሰንሰለት ሽግግር ማሳደግ ላይ ያለመ የምክክር መድረክ በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል።
የ2ኛው የተባበሩት መንግስታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ተሳታፊዎች ዛሬም ወደ አዲስ አበባ በመግባት ላይ ናቸው።
በሰለሞን ከበደ