Search

የዓባይ ወንዝ የኢትዮጵያ ዕውነታ

ማገባደጃው ላይ የሚገኘው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ግንባታ በመስከረም ወር ለምረቃ ይበቃል። በርካቶችም ያችን ቀን በጉጉት ይጠብቋታል። 

ግድቡ ሳይጠናቀቅም እንኳን የኢትዮጵያን ገፅታ መገንባት የቻለ ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን የሚገልጹት የኪንግስ ኦፍ ዓባይ (KoA) ሚዲያ መስራችና /ሥራ አስኪያጅ ዛሂድ ዘይዳን ናቸው። 

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ከመገንባት ባለፈ የአገራችን ገፅታ መገንባት ተችሏል ሲሉ ያስረዳሉ

የዘመናችን ዓድዋ የሆነው የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ከዕለት ጉርሳቸው ቀንሰዉ የሰሩት መሆኑንም ነው የተናገሩት።

‎ዓባይን አስመልክቶ በተለይም "ግድቡ የእኔ ነው" (It’s my dam) በሚለው ንቅናቄ ከገቢ ማሰባሰቢያ ባሻገር የዓባይ ወንዝ ባለቤትነታችንን ለዓለም አቀፍ ማኀበረሰብ ያሳየንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በንቅናቄው ወቅት በአውስትራሊያ ነዋሪ ከነበሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች የተገኘች ተማሪ በፈተና ጥያቄ ወቅት የዓባይ ወንዝ የኢትዮጵያ ነው በሚለው ምላሿ ምክንያት ፈተናው ሲታረም ስህተት ነሽ መባሏን አስታውሰዋል። ይህ አይነት የተዛቡ መረጃዎችን በመጋፈጥ የተሻለ የገጽታ ግንባታ ስራ መከናወኑንም አንስተዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ግን ለመምህራን ብሎም ለተማሪዎች ዕውነታውን ማስረዳት ስለመቻሉ ታራኩን ዋቢ አድርገው ገልፀዋል።

ይህም የነበረውን የገፅታ ሽግግር ለማምጣት የተሄዱ እርምጃዎች ፍሬያማ  መሆናቸው የታየበት አንዱ መንገድ መሆኑን ነው የተናገሩት። 

ግድቡን "የኢትዮጵያ የለውጥ እጥፋት ነው" በማለት የሚገለፁት ዛሂድ ዘይዳን ፤ የግድቡን ግንባታ ሀሳብ ሲቃወሙ የነበሩ አካላት በገንዘብ እስከማገዝ የደረሰ የአስተሳሰብ ለውጥ መፍጠር መቻሉን አክለዋል።

በቀጣይ ዘመኑ የዋጀውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና መሰል ቴክኖሎጂ በመጠቀም በዓባይ ላይ ያለንን ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል ሲሉ ገልፀዋል።

 

በአፎሚያ ክበበው