Search

የቶምቦላ ሎተሪ እድለኛው አቶ ቶምቦላ ወልደ ሥላሴ

በቅርቡ በወጣው የቶምቦላ ሎተሪ የ2ኛው እጣ አሸናፊ የሆነው አቶ ቶምቦላ ወልደ ሥላሴ ስሙ እና እድለኝነቱ መገጣጠሙ ብዙዎችን አስገርሟል።
አቶ ቶምቦላ ወልደ ስላሴ 1984 በይርጋጨፌ ወረዳ ሃሩ ቀበሌ ነው የተወለደው።
ቶምቦላ የተባለበት ምክያትንም ሲያስታውስ፤ እናቱ እሱን ለመውለድ ለረጅም ቀናት ምጥ ይዟቸው እንደቆዩ እና ቡና ነጋዴ አባታቸውም በዚህ ምክንያት ሥራቸውን ትተው ከእናታቸው ጋር እንደነበሩ ይገልጻል።
በዚህ መካከል አባታቸው የሚነግዱት ቡና ቢዘረፍም ባለቤታቸው ከአስጨናቂ ምጥ በኋላ ወንድ ልጅ ስለወለዱላቸው፤ ሀብት ነገ ይተካል እኔ ልጄ ሎተሪ ሆኖልኛል ብለው ቶምቦላ ብለው ስም ያወጡለታል።
አቶ ቶምቦላ አባታቸው ለረጅም ጊዜ ሎተሪ ይቆርጡ እንደነበርም ያስታውሳል። በተለይም በጊዜው በኢትዮጵያ ሬዲዮ የአሸናፊ እጣ ቁጥሮች ሲነገሩ በጉጉት ጠብቀው ያዳምጡ እንደነበርም ይገልጻል።
እርሱም ሎተሪ መቁረጥን ከአባቱ አይቶ እንደጀመረ ገልጾ፤ የረጅም ጊዜ የሎተሪ ደንበኛ እንደሆነ ለኢቢሲ በሰጠው ቃል ገልጿል።
በቅርቡ የውጣው ቶምብላ ሎተሪ ሁለኛ እጣ የባለሁለት መኝታ መኖሪያ ቤት እና 40 ሺህ በየወሩ ለሁለት ዓመት አሸናፊ የሆነበትን እጣ እንዴት እንደቆረጠ ሲያስታውስም፤ በሃሩ ቀበሌ ለምትገኘው ሱቁ አንዳንድ እቃዎች ለማሟላት ከባለቤቱ ጋር ወደ ይርጋጨፌ በመጣበት ወቅት እንደቆረጠ ገልጿል።
እጣው እንደወጣ ለ3 ቀናት አካባቢ ሳያስታውስ ቆይቶ፤ ከ3 ቀን በኋላ ምሽት ላይ አረፍ ብሎ በማሕበራዊ ትስስር ገጽ የእጣ ውጤቱን ሲፈልግ 2ኛ እጣ እንደወጣላት እንደተመለከተም ነው የተናገረው።
ከ12 ዓመት በላይ በየገጠመኙ ሎተሪ ይቆርጥ እንደነበርም አቶ ቶምቦላ ወልደ ሥላሴ ተናግሯል።
በብሩክታዊት አስራት