እናቱ ወይዘሮ ሸምሲያ እንደ “አጋዝ ሲፈኖ” ስምሽን የሚያስጠራ ልጅ ይስጥሽ ተብለው ተመርቀዋል። አጋዝ ሲፈኖ በጉራጌ ሕዝብ ዘንድ ሰሙ የሚታወሰ ጀግና ነው። ወይዘሮ ሸምሲያም ታዲያ እጃቸውን ዘርግተው አሚን አሉ።
ልጃቸው ማሕሙድም የወላጅ እናቱንም፣ የእናት ሀገሩንም ሰም የሚያሰጠራ ሆነ!
“ዕድሜ እና ጤንነት፤ የሰው መውደድ ይስጥህ” ተብሎ በእናቱ የተመረቀው ማሕሙድ ለ60 ዓመታት እንደተወደደ አለ።
አርቲስት ማሕሙድ አሕመድ ልጅነቱን በመርካቶ፣ ሃብተጊዮርጊስ ድልድይ፣ አሜሪካ ግቢ ከዚያም በራስ ዳምጠው ሆስፒታል አካባቢ አሳልፏል፤ የቁርአን እና የቄስ ትምህርቶችንም ቀስሟል።
ዘመናዊ ትምህርትም በአርበኞች እና መስፍን ሐረር ትምህርት ቤቶች የተከታተለ ሲሆን በየዓመቱ የትምህርት መዝጊያ ላይ በወላጆች በዓል ላይ የዘፈን ሥራዎችን ያቀርብ ነበር።
ልቡ ወደ ሙዚቃ በማምራቱ በትምህርቱ መቀጠል ያልቻለው ማሕሙድ፣ አስረስ ይታገሱ እና ጌታቸው ወልደጊዮርጊስ ከተባሉ ልጅነት ጓደኞቹ ጋር በመሆን በሰፈር ሠርግ ሲደገስ ዋነኞቹ አድማቂዎች ሆኑ።
ማሕሙድ ከትምህርቱ መቋረጥ በኋላ ቤተሰቦቹን በገቢ ለመደገፍ ያልሠራው የሥራ ዓይነት የለም። ከጫማ ጠራጊነት እስከ አናፂነት፣ ቀለም ቀቢነት እና ምግብ አብሳይነት ሰርቷል። የሥራ ፍቅሩ እና ታታሪነቱም ከሕልሙ ጋር አገናኝቶታል።
ከአሪዞና ክለብ እስከ ዓለም አቀፍ መድረክ የ60 ዓመት የሕይወት ጉዞ
ረዳት ምግብ አብሳይ ሆኖ በሚሠራበት አሪዞና የምሽት ክለብ የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ሙዚቀኞች እነጥላሁን ገሠሠ፣ ተፈራ ካሣ፣ ሻለቃ ግርማ ሃድጉ የመሳሰሉ ይጫወቱ ነበር።
ክህሎቱን መግለጫ በሆነች ቀንም ድምፃዊያኑ ቀርተው የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾቹ ብቻ በሚጫወቱበት ጊዜ ማሕሙድ ከምግብ ማብሰያው ክፍል በመውጣት የያኔውን ሻለቃ ግርማ ሃድጉን በማስፈቀድ የተፈራ ካሣ እና ተዘራ ኃይለሚካኤልን “አልጠላሽም ከቶ” ተጫወተ፤ ታዳሚውም በደስታ “ቢስ” (ይደገም) በማለት አስደገሙት።
የአሪዞና የምሽት ክለብ ባለቤት ሚስተር ሱብሂን ክሩንፍሌ ረዳት ምግብ አብሳዩን መድረክ ላይ ሲመለከት አላመነም ነበር። ማሕሙድ አጋጣሚውን ተጠቅሞ መክሊቱን ባሳየ ማግስት አዲስ ልብስ ተገዝቶለት ወደ ሙዚቀኝነት ተሸጋገረ። ድምፃዊያኑ እነ ጥላሁን ሲመጡም ወጣቱን ማሕሙድ አድንቀው ወዳጃቸው አደረጉት።
ማሕሙድ በአሪዞና የምሽት ክለብ ከታላላቅ ድምፃውያን ጋር መጫወት በጀመረበት ወቅት ሻለቃ ግርማ ሃድጉ ተወዳጅ ሥራ ሰጡት፤ “ካንቺ በቀር ሌላ ብሞት አልመኝም ግን እስካሁን ድረስ አላወቅሽልኝም” የሚለውን ሥራ። ይህ ሙዚቃ በኋላ በክቡር ዘበኛ ለመቀጠር ያቀረበው የመጀመሪያው ሙዚቃው ሆነ።
በ1955 በ60 ብር ደመወዝ በክቡር ዘበኛ የተቀጠረው ማሕሙድ አሕመድ ለ11 ዓመት ከ2 ወራት ከታላላቆቹ ጋር ድንቅ ሥራዎችን ሲያቀርብ ቆየ።
“የትዝታው ንጉሥ” ያሰኘውን ትዝታ መጫወት የጀመረው በአስኮ አክሱም አዳራሽ በ1957-58 ዓ.ም ነው፤ ከዚያ በኋላ ትዝታ እና ማሕሙድ አልተለያዩም።
“የሺ ሃረጊቱ” የተሰኘው ሙዚቃውም ከሕዝብ ጋር ይበልጥ አስተዋወቀው።
ራስ፣ ዋቢ ሸበሌ፣ ጊዮን፣ ሂልተን እና ሌሎች ታዋቂ ሆቴሎች ማሕሙድን ተሻሙበት።
ከክቡር ዘበኛ ወደ አይቤክስ፣ ከአይቤክስ ወደ ዋልያስ፣ ከዋልያስ ወደ ሮሃ እየተዘዋወረ ሲጫወትም “ማሕሙድ የሌለበት መድረክ አይደምቅም!” ተባለ።
የትዝታው ንጉሥ የመጀመሪያውን ሸክላ በአመሃ እሸቴ አማካኝነት ከቬነስ ባንድ ጋር በሸክላ አሳትሟል። 2ኛ እና 3ኛ ሸክላውን ደግሞ በአይቤክስ ባንድ አጃቢነት፤ በአመሃ እሸቴ አሳታሚነት በ1965 ለሕዝብ አድርሷል።
ማሕሙድ በ1972 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሜሪካ የተጓዘ ሲሆን ከቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ጋር ወደ ጅቡቲ እና ኬንያ በመጓዝ ሥራዎቹን ማቅረብ ችሏል።
ከሕዝብ ለሕዝብ ኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ጋር በመጓዝም በሦስት አህጉራት በ18 ሀገራት ሥራዎችን አቅርቧል።
ከፍራንሲስ ፋልሴቶ ጋር ከተዋወቀ በኋላ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ተጫውቷል።
ከአሪዞና የምሽት ክለብ ተነሥቶ ምዕራባውያኑን “አቤት፤ አቤት” በማሰኘት የኢትዮጵያ የሙዚቃ አምባሳደርነቱን አሳይቷል።
ማሕሙድ አብረውት ለሠሩት ብቻ ሳይሆን ለአዳዲስ ተተኪዎች ፍቅሩን ዝቅ ብሎ በአደባባይ ለመግለጽ የማይሰስት፣ ዝቅ በማለቱ የሚከበር የትህትና ምልክት የሆነ አርቲስት ነው።
ከዓሊ ቢራ፣ ፀሐዬ ዮሐንስ፣ ጎሣዬ ተስፋዬ እና ሌሎች የሙያ አጋሮቹ የሠራቸው የኅብረት ሙዚቃዎችም ጥበብ ብቻ ሳይሆን ሰው ወዳጅነቱን ያሳያሉ።
በስሙ የሚጠራ፣ የፒያሳ ምልክትና መቀጣጠሪያ የነበረ ማሕሙድ ሙዚቃ ቤትንም ከፍቶ ነበር።
ማሕሙድ ስለ ኢትዮጵያ “የደፈረሽ ይውደም” ብሎ የሀገር ፍቅሩን በዜማ ገልጿል፤ ሰላም ዋጋዋ ትልቅ መሆኑንም “ሰላም ለዓለማችን” የሚል እንደ ብሔራዊ መዝሙር ሊዘመር የሚገባው ዘፈን አቀንቅኗል።
ማሕሙድ እግር ኳስ ወዳጅ ነው፤ በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ልምምድ ሲያደርግ አብሮ ያደርግ ነበር። በረኛ ሆኖ የተጫወተው ማሕሙድ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊ ሲሆን ከይድነቃቸው ተሰማ ጋር ወዳጅ በመሆኑ ከቡድኑም ጋር ልምምዶችን ያደርግ እንደነበር ይነገራል።
የትዝታው ንጉሥ ከነሂሩት በቀለ ጋርም ቴአትር ሠርቶ ሁለገብ ባለሙያ መሆኑን አሳይቷል።
የአፍሪካ ሙዚቃ አምባሳደር ማሕሙድ አሕመድ በተለያዩ ጊዜ ሽልማቶችን እና ዕውቅናዎችን ያገኘ ሲሆን ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለ60 ዓመታት አበርክቶው የክብር ዶክትሬት ሰጥቶታል። ቢቢሲም በ1999 ዓ.ም የወርልድ ሚዩዚክ አዋርድን ሸልሞታል።
የኢቢሲ የመዝናኛ መሰናዶ የሆነው “እሑድ ቤት” ቤተሰቦች በዚያራ ዝግጅት አርቲስት ማሕሙድ አሕመድን ዘይረውታል፤ አርቲስቱ በአዲስ አልበም ጠብቁኝ ሲል ነግሯቸዋል።
እሑድ ቤት በዚያራ ዝግጅቱ ከአርቲስት ማሕሙድ አሕመድ ጋር ያደረገውን ቆይታ ይመልከቱ!
በፋሲካው ታደሰ
#EBC #ebcdotstream #Mehamud #tizita #music