በተጨማሪም ለደቡብ አፍሪካ የምታደርገውን የውጭ ዕርዳታ በማቋረጥ ተጨማሪ የ30 በመቶ ታሪፍ እንደምትጥልባት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጠቁመው ነበር።
ይህም ብቻ አይደለም አሜሪካ በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ነጭ ዜጎች ላይ ይፈጸማል ባለችው በደል እና 'የዘር ማጥፋት' የተነሣ የሀገሪቱን መንግሥት ክፉኛ ስትወነጅል ሰንብታለች።
በእርግጥም በአፍሪካ ጉዳዮች በአንፃራዊነት ሰፊ ትኩረት የለውም የሚባለው የትራምፕ አስተዳደር በደቡብ አፍሪካ ላይ ባልተለመደ መልኩ ትኩረት ሲያደርግ መቆየቱን ብዙዎች ይናገራሉ።
ሁለቱ ሀገራት በእስራኤል እና ፍልስጤም ጉዳይ ላይ ሰፊ ልዩነት ያላቸው ሲሆን፣ የደቡብ አፍሪካ የብሪክስ መሥራች አባልነት እና ከሩሲያ ጋር ያላት እንቅስቃሴም አሜሪካን እንደሚያሳስባት ‘ካውንስል ኦፍ ፎሬይን ሪሌሽንስ’ የተሰኘው እና በፖለቲካ እና የውጭ ጉዳይ ግንኙነቶች ላይ አተኩሮ የሚሠራው አማካሪ ቡድን ባወጣው ጸሑፍ አስነብቧል።
ይህን ሁሉ ውጥረት ያረግባል ተብሎ የተጠበቀውን ውይይት ለማድረግ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ወደአሜሪካ አቅንተው ነበር። ራማፎሳ ዋሽንግተን የደረሱት የትራምፕን ለማግባባት አስበው እንደሆነ በስፋት ሲዘገብ ቆይቷል።
ለዚህም ከትራምፕ ጋር ቀረቤታ አላቸው ተብለው የሚታሰቡትን ነጭ የጎልፍ ተጫዋቾቹን ኤርኒ ኤልስ እና ሬቲፍ ጉሰን እንዲሁም ነጩን ደቡብ አፍሪካዊ ቢሊየነር እና የቅንጦት ዕቃዎች ነጋዴውን ዮሃን ሩፐርትን ይዘው ነው በኋይት ሐውስ የተገኙት።
ይሁንና የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ውይይት እንደተጠበቀው ሳይሆን አለመግባት የተስተዋለበት እንደነበር ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ይገኛሉ።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በነጩ ቤተመንግሥት የትራምፕ ቢሮ በሰላምታ ቢጀምሩም በመሐል ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ ዶናልድ ትራምፕ ዝግጅት ባደረጉበት አግባብ ረዳታቸውን መብራቶቹን እንዲቀንሱ እና ቴሌቪዥኑን እንዲከፍቱ አዘዙ።
ቴሌቪዥኑ ሲከፈትም በደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ ይፈጸማል ስለተባለው ጥቃት እና የተለያዩ ችግሮች የሚያወሱ ዜናዎች እና ጥያቄዎችን የያዙ ቪዲዮዎች ይታዩ ጀመር።
ያኔ በደቡብ አፍሪካ የተወለደው አሜሪካዊው ቢሊየነር ኢሎን መስክ፣ ከሶፋ ጀርባ ሆኖ በፀጥታ ይመለከት ነበር።