Search

አረንጓዴ ልማትን የህልውናቸው ጉዳይ ያደረጉ ሀገራት

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እየተፈተኑበት ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም ደንን መልሶ የማልማት ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ እነዚህ ሀገራት ባደረጉት የተሳካ ጥረትም የደን ሽፋናቸውን ለማሻሻል ከመቻላቸውም በተጨማሪ ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል። ይህ ጥረታቸውም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ በተከታታይ በሠሯቸው የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ስኬታማ የሆኑ ጥቂት ሀገራትን እንመለከታለን፡፡

1.    የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ

ከ40 ዓመታት በፊት ከ30 በመቶ በላይ የነበረው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በሂደት ተመናምኖ አንድ ወቅት እስከ 3 በመቶ ወርዶ ነበር፡፡

ሁኔታው ያሳሰባቸው የኢትዮጵያ መንግሥታት ችግኞችን በመትከል አስፈሪውን የደን መመናመን ለመቀነስ ሙከራ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በዚህም ከ2011 ዓ.ም በፊት የነበረው የደን ሽፋን ወደ 17.2 በመቶ ደርሶ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ከስድስት ዓመታት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ከቀድሞዎቹ በተለየ ትኩረት እና ቀጣይነት ባለው መልኩ እየተሠራ ተጨባጭ ውጤቶችን እያመጣ ይገኛል፡፡

በዚህም እንቅስቃሴው ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ 40 በሊዮን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ ቀድሞ የተራቆቱ አካባቢዎች አረጓዴ ካባ እየለበሱ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየሠራች ባለችው ሥራ ዕውቅናን አግኝታበታለች፡፡

የኢትዮጵያ ደን ሽፋን ከ2011 በፊት ከነበረበት 17.2 በመቶ ከ23 በመቶ በላይ ማደጉን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ኮንቬንሽን ባለፈው ዓመት አረጋግጧል፡፡

ይህ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ የለም አፈር መከላትን ከ1.9 ቢሊየን ወደ 208 ሚሊየን ቶን ዝቅ እንዲል አስችሏል፡፡ አሁን የደረሰችበትን የደን ሽፋንም በ2030 ወደ 30 በመቶ ለማድረስ እየሠራች ትገኛለች።

በዚህ ዓመት "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ቃል 7.5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል መርሐ-ግብር ወጥቶ ሥራ የተጀመረ ሲሆን፣ በነገው ዕለት በአንድ ጀምበር 700 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብር ተይዟል፡፡

2.    ቻይና "ታላቁ አረንጓዴ ግንብ"

ቻይና በረሃማነትን ለመዋጋት እና የአፈር መሸርሸርን ለመቀነስ በተለይም በ"ታላቁ አረንጓዴ ግንብ" ፕሮጀክት ግዙፍ የደን ከፍተኛ የደን መልሶ ማልማት ሥራን አከናውናለች።  ከአውሮፓውያኑ 1978 ጀምሮ ፕሮጀክቱን እየተገበረችው ያለችው ቻይና የደን ሽፋኗ በእጅጉ ጨምሯል። "ሰብል ለአረንጓዴ" የሚለው መርሐ ግብሯ ደግሞ አርሶ አደሮቿ የሰብል መሬትን ከደን ልማት ጋር አሰናስለው ምርታማ እንዲሆኑ በማድረግ ስኬታማ የሆነችበት አንዱ ዘዴዋ ነው።

3.    የአፍሪካ "አረንጓዴ ግድግዳ"

ይህ ትልቅ ፕሮጀክት በአፍሪካ ከሳህል ቀጣና እስከ ጂቡቲ ያለውን የአፍሪካ ክፍል የሚያካልል ነው፡፡ ዓላማውም የተራቆተውን መሬት መልሶ ማቋቋም፣ በረሃማነትን መዋጋት እና የምግብ ዋስትናን ለማሻሻል ነው። ኢትዮጵያ የዚህ ጥረት አካል በመሆን በአረንጓዴ አሻራ መጠነ ሰፊ የደን ልማት መርሐ ግብርን ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች። እንደ ሩዋንዳ፣ ካሜሩን እና ኮንጎ ሪፑብሊክ ያሉ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም የዚህ ፕሮጀክት አካል በመሆን የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።

4.    ሕንድ

ሕንድ በዓለም ላይ በደን ልማት እርምጃ ስኬታማ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን፣ በ2030 ከ2.5 እስከ 3.0 ቢሊዮን ቶን ካርቦንዳይኦክሳይድን ለማስቀረት እንደቻለች መረጃዎች ያመላክታሉ። በከተሞች ውስጥ የምትተገብራቸው የ"ሚያዋንኪ" ዘዴ ደግሞ ለውጤታማነቷ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይገለጻል፡፡ የቶዮታ ኩባንያን በመተው ወደ ደን ልማት ፊቱን ባዞረው ልጇ ሹብሄንዱ ሻርማ የተጀመረው "ሚያዋንኪ" ዘዴ የሀገር በቀል ዕፅዋት ላይ ተመስርቶ ጥቅጥቅ ያሉ እና በፍጥነት የሚያድጉ እንዲሁም ብዝኃነት ያላቸው ዛፎችን በመትከል ላይ የሚያተኩር ነው።

5.    ደቡብ ኮሪያ

ደቡብ ኮሪያ በአንድ ወቅት ከፍተኛ የደን መጨፍጨፍ ያራቆታት ሀገር ነበረች፡፡ ከ1950ዎቹ ጀምሮ በመንግሥቷ በተወሰደ ተከታታይ እርምጃ ግን የደን ሽፋኗን ከ63 በመቶ በላይ ማሳደግ ችላለች።

6.  ኮስታሪካ

ኮስታሪካ በአካባቢ ጥበቃ እና ደን ልማት ባመጣችው ተጨባጭ ለውጥ የዓለማችን ስኬታማው ሀገር እስከመባል የደረሰች ሀገር ነች፡፡ የደን ሽፋንዋን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ በ2021 ወደ 60 በመቶ ገደማ ሊደርስ ችሏል፡፡ ሀገሪቱ መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ ፖሊሲዎችን ቀርጻ በመንቀሳቀስ እና የመሬት አጠቃቀም ልምዶችን በመቀመር ነው ይህን አስደናቂ ለውጥ ያመጣችው፡፡ 

7.    አውሮፓ

የአውሮፓ ሕብረት ሀገራት ከ2000ዎቹ ጀምረው ባደረጉት የደን ልማት እንቅስቃሴ በርካታ የተራቆቱ አካባቢዎች በደን መሸፈን ችለዋል፡፡ አየርላንድን፣ ፖላንድን፣ ዴንማርክን እና ኔዘርላንድን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ ሀገሮች የደን ልማቱ ፕሮጀክት ተሳታፊዎች ናቸው።

8.   ኮሎምቢያ "ቪቻዳ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ"

ኮሎምቢያ "ቪቻዳ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ" የሚል ፕሮጀክት ቀርጻ ነው የደን ልማት ላይ እየሠራች ያለችው፡፡ የካርቦን ልቀትን ለመከላከል እና ለሥነ ምህዳራዊ መረጋጋት ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ጠንካራ የዛፍ ዝርያዎች ትተክላለች፡፡ በዚህም ቀድሞ የተራቆቱ አካባቢዎችን ደን በማልበስ እና የደን ጭፍጨፋን በማስቀረት ውጤታማ ሆናለች።

9.    ኢንዶኔዥያ "ቦርኒዮ የደን ልማት ፕሮጀክት "

የኢንዶኔዥያ የደን ልማት ፕሮጀክቶች የሚያተኩሩት የሀገሬው የዛፍ ዝርያዎች ያለባቸውን የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ከንክኪ በመጠበቅ ላይ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ አብዛኛውን ጊዜ አነስተኛ አርሶ አደሮችን ያካተተ እና ዛፎቹ ለእነሱ የሚሰጡአቸው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን በመለየት ይተገበራል። ፕሮግራሙ መንግሥት እና ማኅበረሰብን አጣምሮ የሚያሳትፍ ሲሆን፣ ዘላቂ የመሬት አስተዳደር ልምዶችን እና  አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንም ይጠቀማል።