Search

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት - ኢትዮጵያ አገልግሎትን ለማሻሻል ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያ

በመንግሥት ተቋማት ብዙዎች ከሚማረሩባቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የአግልግሎት አሰጣጥ አለመዘመን ነው።  አንድን አገልግሎት ለማግኘት ያለው መባከን የአገልግሎት ፈላጊውን ውድ ጊዜ እና ጉልበት የሚበላ ነው።

ከመጠን ያለፈ የወረቀት ሥራ እና አዝጋሚ ውሳኔ አሰጣጥ፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን ማዘግየት፣ ደካማ የተቋማት ቅንጅት በዘርፉ የሚታይ የአገልግሎት አሰጣጡን ኋላ ቀርነት ማሳያ ነው።

በመሬት አስተዳደር፣ በፍቃድ አሰጣጥ እና በግዥ ላይ ጉቦ እና ሌብነት መንሰራፋት፣ የተጠያቂነት አለመኖር፣ የፀረ-ሙስና ሕጎች ደካማ አፈፃፀም ኋላቀር በሆነው አሠራር ምክንያት የሚከሰቱ ናቸው።

ይህ ዓይነት አካሄድም ተገልጋዮችን በማማረር ሕዝብ ከመንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት ያበላሻል። የሀገርን ሀብት እና ጊዜ በማባከን ወደ ውድቀት ያመራል። ድምሩ የመልካም አስተዳደር ችግር ይሆናል።

በአንጻሩ ደግሞ የተሻሻለ እና የዘመነ የሕዝብ ተቋማት የፈጠሩ ሀገራት ቀልጣፋ፣ ተጠያቂነት ያለው፣ ሁለንተናዊ እና በዜጎች ዘንድ ተአማኒነት የሚፈጥሩ አግልግሎት ይሰጣሉ። እንደዚህ ዓይነት ተቋማት በገነቡት ሀገራት መንግሥት እና ሕብረተሰብ መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ ይሆናል።

ኢትዮጵያ የተቋማዊ ሪፎርም ከጀመረች ቆይታለች። በሪፎርሙ እንዲሻሻሉ ትኩረት ከተደረገባቸው ዘርፎች መካከል ደገሞ የአገልግሎት አሰጣጡ ይገኝበታል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተከፈተውም ለዚህ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለፓርላማ ባቀረቡት ማብራሪያ ላይ እንደገለጹት መሶብ የኢትዮጵውያን የባህል መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው፣ ፕሮጀክቱ ቤተሰብ በአንድ መሶብ ዙሪያ ተሰባስቦ እንደሚመገበው ሁሉ አገልግሎት ፈላጊዎች በአንድ ማዕከል በርካታ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

ማዕከሉ በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል። ማዕከሉን ከፍተው ሥራ ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሶብ የቆየ እና የተጎዳ ህንፃን ወደ ዘመናዊ እና ሥነ-ውበታዊ ደረጃው ለሥራ ከባቢ አስደሳች ወደ ሆነ ህንፃ እንደተለወጠ ጠቅሰዋል።

አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል ለማሰባሰብ እና ለማቀናጀት በሀገር ውስጥ የለማ ሶፍትዌር በሥራ ላይ መዋሉንም ገልጸዋል። በታደሰ አመለካከት ብቁ እና ክብር የሞላበት አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች መዘጋጀታቸውንም አውስተዋል።

በርካታ ተቋማት የሚሰጡአቸውን አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል ያሰበሰበው መሶብ ቤተሰብ አንድ ማዕድ ተሰብስቦ እንደሚመገበው ሁሉ ዜጎች ፈጣን አገልግሎት የሚያገኙበት ነው።