በፎርብስ መረጃ መሠረት አጠቃላይ ሃብታቸው 116.3 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።
ይሁንና በውድ ጌጣጌጦች ተውቦ መሽቀርቀር እና ልታይ ልታይ ማለትን እምብዛም አይወዱም።
ቀለል ባለ አለባበስ እና በተለመደችው የንባብ መነጽራቸው የሚታወቁት ቢል ጌትስ በበርካታ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ይሳተፋሉ።
በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ከሚኖራቸው ሃብት ውስጥ 99 በመቶውን ለደሃ ሀገራት ለመለገስም ወስነዋል።
አሜሪካዊ የኮምፒውተር ፕሮግራመር እና ሥራ ፈጣሪው ቢል ጌትስ የተወለዱት እ.አ.አ. በወርሃ ጥቅምት 1955 ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ነው።
በ13 ዓመታቸው የመጀመሪያውን የሶፍትዌር ፕሮግራማቸውን እንደጻፉም በአንድ ወቅት ተናግረዋል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤታቸውን የደመወዝ አከፋፈል ሥርዓት በኮምፒውተር የሚያደራጅ የፕሮግራመሮች ቡድን እንዲቋቋም በማገዛቸውም ይወደሳሉ።
ከዚህ ባለፈ ከጓደኛቸው ፓውል አለን ጋር ለሀገር ውስጥ አስተዳደሮች የትራፊክ መረጃ ሥርዓቶችን የሚያቀርብ ትራፍ-ኦ-ዳታ (Traf-O-Data) የተሰኘ ኩባንያም መሥርተው እንደነበር ግለ ታራካቸው ያስረዳል።
በኋላም የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲን የተቀላቀሉት ቢል ጌትስ እ.አ.አ በ1975 የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሳሉ ከፓውል አለን ጋር ለመጀመሪያዎቹ ማይክሮ ኮምፒውተሮች ሶፍትዌር ለመሥራት ተጣመሩ።
ይህ ፕሮጀክት በተሳካ ሁኔታ ከተጠናቀቀ በኋላ ጌትስ በሦስተኛ ዓመታቸው ሃርቫርድን ለቅቀው ወጡ። ከዚያም ከአለን ጋር በመሆን ማይክሮሶፍትን ለመመሥረት መብቃታቸውን ታሪካቸው ያስረዳል።
ጓደኛቸው በሕመም ምክንያት ማይክሮሶፍትን ለቅቆ ሲወጣ ሙሉ ኃላፊነቱን በመውሰድ ኩባንያውን መምራት ቀጠሉ። በኋላም ማይክሮሶፍት ትልቁ የግል ኮምፒውተር ሶፍትዌር ኩባንያ እየሆነ ሲመጣ ቢል ጌትስ የዓለማችን ባለጸጋ መሆን ችለዋል።
የበጎ አድራጎት ሥራ
እ.አ.አ በ1994 ከቀድሞ ባለቤታቸው ሜሊንዳ ጋር በመሆን ዓለም አቀፍ የጤና ፕሮግራሞችን እንዲሁም በፓስፊክ ሰሜን ምዕራብ ያሉ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ ለመደገፍ የዊልያም ኤች. ጌትስ ፋውንዴሽንን አቋቁመዋል። በኋላም የፋውንዴሽኑ ስም ወደ ቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ቀይረውታል።
ድርጅቱ ባደረገው ድጋፍ በበርካታ ሀገራት የክትባት አቅርቦትን በማሳደግ፣ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ስርጭትን በመከላከል፣ የቲቢ እና የወባ በሽታ ወረርሽኝን በመቀነስ ረገድ ገንቢ ሚና ተጫውቷል።
ቢል ጌትስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፖሊዮ፣ በወባ፣ በኩፍኝ አማካኝነት የሚከሰቱ የእናቶችን እና የጨቅላ ሕፃነትን ሞት ለማስቀረት ፍላጎት እንዳላቸው ይናገራሉ።
በፋውንዴሽናቸው በኩልም ባለፉት 25 ዓመታት 100 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለግሰዋል። ቢል ጌትስ እ.አ.አ በ2026 በዓለም የጤና ዘርፍ የሚያደርጉት ድጋፍ እስከ 9 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚደርስ የቢቢሲ ዘገባ ያመላክታል።
የ69 ዓመቱ ቱጃር በቅርቡ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ በነበረ ጉባዔ ላይ ተገኝተው በዓለም ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊፈቱ የሚገባቸው ብዙ ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል።