በኢትዮጵያ፡-
"ኧረ ልጆች፣ ልጆች እንጫወት በጣም፣
ከእንግዲህ ልጅነት ተመልሶ አይመጣም፣
ልጅነቴ፣ ልጅነቴ ማር እና ወተቴ፤ …" የሚል የሕፃናት መዝሙር አለ።
ለመሆኑ ይህን መዝሙር እንዴት ነው የምንገነዘበው? ልጆቻችን ተመልሶ የማይመጣውን የልጅነት ጊዜያቸውን እንዲጠቀሙ ምን ያህል እንረዳቸዋልን?
ጨዋታ የልጆች ዋነኛ መብት መሆኑንስ ስንቶቻችን እናውቃለን? ልጆቻችን ንቁ ሆነው ቤት ወስጥ ሲንቀሳቀሱ፣ “ረበሹ” ብለን እንማረርባቸዋለን ወይስ “የጤንነት ምልክት ነው” ብለን እንደሰታለን? ጨዋታ ጠግቦ ባደገ ልጅ እና በቂ የጨዋታ ዕድል ባላገኘው ልጅ መካከል ያለውን የአዕምሮ ንቃት እና ዕድገትስ ስንቶቻችን አስተውለን እናውቃለን? ለልጆቻችንስ የምንመርጠው ጨዋታ ምን ዓይነት ነው?
ከሕፃናት መብቶች ቀዳሚው፣ በቂ የጨዋታ ጊዜ እና የመጫወቻ ዕድል ማግኘት ነው። ጨዋታ ልጆች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት መንገድ ብቻ ሳይሆን፤ በሁሉም ረገድ ጤናማ ዕድገት እንዲኖራቸው የሚያስችል መሠረታዊ እና ወሳኝ ጉዳይ ነው።
የሰው ልጆችን ዕድገት የሚተናትነው "Developmental Psychology"፣ ልጆች በየደረጃቸው መጫወት የሚገባቸው ጨዋታ ካልተጫወቱ ጫናው እስከ እርጅና ባለው የዕሜያቸው ደረጃ እንደሚከሰት እና ፈተና እንደሚሆንባቸው ይተነትናል።
"Developmental Psychology" ከሚዘረዝራቸው ስምንት የሰው ልጆች የዕድገት ደረጃዎች አምስቱ የሕፃናትን ዕድገት የሚመለከቱ መሆኑ ለሕፃናት ዕድገት ምን ያክል ትኩረት መደረግ እንዳለበት ማሳያ ነው።
በትክክለኛ ዕድሜያቸው ትክክለኛውን ጨዋታ የተጫወቱ ልጆች ጠንካራ የአዕምሮ፣ አካላዊ፣ ማኅበራዊ እና የስሜት ዕድገት ይኖራቸዋል። እንደዚህ ዓይነቶቹ ልጆች ደግሞ ለቤተሰብ፣ ለማኅበረሰብ፣ ለሀገር እልፎም ለዓለም የሚጠቅሙ ዜጎች የመሆን ዕድላቸው የሰፋ ነው።
ይህን አስፈላጊ የዕድገት ደረጃ የተረዳው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰኔ 4 ቀን (በፈረንጆቹ ጁን 11) በየዓመቱ የጨዋታ ቀን ተብሎ እንዲሰየም ወስኗል።
"መጫወት ልጆች የደኅንነት፣ እንክብካቤ እና ፍቅር እንደሚሰጣቸው የሚያረጋግጡበት ምልክት ነው፤ በቂ የጨዋታ ጊዜ ካገኙ ከባድ ችግር ውስጥ በሚገቡበት ጊዜም እንኳ የሚጠብቃቸው እንዳለ እንዲያስቡ ያስችላቸዋል" ይላሉ የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራስል።
የጨዋታ ቀን እንዲኖር የሚያስፈልገው ሁሉም ሰው ልጆች በቂ የጨዋታ ዕድል ሲያገኙ የሚጠበቅባቸውን ፍሬ እንዲያስገኙ በማሰብ ለልጆች በቂ የጨዋታ ዕድል እንዲፈጠር ታስቦ እንደሆነ በድርጅቱ ድረ-ገጽ የወጣው መረጃ ያመላክታል።
ጨዋታ ከመዝናኛ አልፎ ሰዎች የሚግባቡበት ከብሔራዊ፣ ባህላዊ እና ማኅበረዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ድንበሮች የተሻገረ ዓለም አቀፋዊ ቋንቋ ነው።
ጨዋታ የሰዎችን ጥንካሬ፣ ችሎታን፣ የፈጠራ ክህሎት እና አዳዲስ ነገሮችን የማሰብ አቅም ያጎለብታል። በተለይ ደግሞ ልጆች ከሌሎች ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዲጠናከር፣ የስሜት ቀውሶችን እንዲቋቋሙ እንዲሁም ችግሮችን የመፍታት አቅማቸውን እንዲያደብሩ ይረዳቸዋል።
የልጆችን የመጫወት ዕድል መገደብ ደኅንነታቸው እና ዕድገታቸው ላይ ቀጥታ ተፅዕኖ ያሳድራል። በጨዋታ የተደገፈ ትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ልጆች ትምህርታቸውን በንቃት እንዲከታተሉ የሚያደርግ ውጤታማ ዘዴ መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል። በዚህ መልክ የሚሰጠው ትምህርት ይበልጥ አስደሳች እና ጠቃሚ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ አዕምሮአቸው መረጃን በሥርዓት እንዲያደራጅ ይረዳል።
በተጨማሪም ጨዋታ መቻቻልን፣ ጥንካሬን፣ ማኅበራዊ አካታችነትን፣ ግጭትን መከላከል እና ሰላምን ማጎልበት ላይ በጎ ተፅዕኖ ያለው ትውልድ እንዲፈጠር ያስችላል።
ይህን እውነታ ከግምት በማስገባት ነው ተመድ የሕፃናት መሠረታዊ መብቶች በሚደነግገው ቻርተሩ አንቀፅ 31 መሠረት ለእያንዳንዱ ሕፃን መሠረታዊ መብት ሆኖ የመጫወት መብትን ያፀደቀው።
የዚህ ዓመት ዓለም አቀፍ የጨዋታ ቀን መሪ ቃል "በየቀኑ ጨዋታን ይምረጡ" የሚል ነው። መሪ ቃሉ መንግሥታት፣ የንግድ ድርጅቶች፣ ትምህርት ቤቶች እና ቤተሰብ የልጆች ጨዋታን እንዲያበረታቱ እና ቅድሚያ በሚሰጡ ውሳኔዎች ውስጥ እንዲያካትቱት የሚያሳስብ ነው።
ባለፈው ዓመት የተጀመረው ዓለም አቀፉ የጨዋታ ቀን በብሔራዊ እና በአካባቢ ደረጃ የመጫወትን አስፈላጊነት ከፍ ለማድረግ ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ የተጀመረ ነው።
ዕለቱ ጨዋታን በዓለም ዙሪያ በትምህርት እና በማኅበረሰባዊ ሁኔታዎች ውስጥ ለማካተት ፖሊሲዎች፣ ሥልጠናዎች እና የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ የሚቀርብበትም ነው።
በለሚ ታደሰ