ወላይታዎች “ሊያድር የነበረውን ምግብ ዳታ ጨረሰው” ይላሉ

2 Days Ago 205
ወላይታዎች  “ሊያድር የነበረውን ምግብ ዳታ ጨረሰው” ይላሉ

የጦና ልጆች አንድ አባባል አላቸው፡፡‘’አቃና ካታ ባምባሬ ውረሴስ’’ይላሉ በወላይትኛ፤ ትርጉሙም ሊያድር የነበረውን ምግብ ዳታ ጨረሰው እንደማለት ነው።

አባባሉ በማቃጠል ባህሪው የሚታወቀው ዳታ (በተለምዶ ዳጣ ተብሎ የሚጠራው) የምግብ ፍላጎትን የመጨመር ከፍተኛ አቅም እንዳለው ያመላክታል።

በልዩ ጣዕሙ የሚታወቀው ዳታ በወላይታ በአብዛኛው ቤት ከገበታ ጋር አብሮ ከመቅረቡም በላይ ከጥሬ ስጋ ጋር ማባያ ተደርጎ ይዘወተራል።

ብዙውን ጊዜ ዳታ የአካባቢው የባህል ምግብ ከሆኑት ጎደሬ፣ ቦዬ እንዲሁም በድንች ከሚሰሩ ማዕዶች ጋር ይቀርባል።

ልምድ ባላቸው ጎበዝ የባህል ምግብ ባለሙያ ሴቶች አማካኝነት ጥራት ያለውን ዳታ ለማዘጋጀት፤ እሸት ቃሪያ ወይም ደረቅ በርበሬ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ የወላይታ ቀይ ሽንኩርት፣ በሶብላ፣ ኮሮሪማ፣ ዝንጅብል እና ጨው ያስፈልጋል።

ዳታን ከቀይ እና ከእሸት አረንጓዴ ቃሪያ ማዘጋጀት ይቻላል። በመጀመሪያ የተዘጋጀው ቃሪያ ይቀነጠሳል፣ ቀጥሎም ይታጠብና ድቅቅ ተደርጎ ይዳጣል።

ከዚያም ለግብዓትነት የተዘጋጁ ቅመማቅመሞች ለየብቻ ይዳጣሉ።

በማስከተል ነጭ ሽንኩርቱና በሶብላውን የማዋሃድ ሥራ ይከናወናል።

ቀጥሎም በመጠኑ ጨው እየተጨመረበት እንደገና በደምብ እንዲደቅ ተደርጎ ቃሪያው እና ቅመማ ቅመሞቹን እንደገና ሁሉንም አንድ ላይ በማዋሃድ ይዳጣል።በመጨረሻም ጣዕሙ ተቀምሶ በተዘጋጀለት ማስቀመጫ ይደረጋል።

እንደየአስፈላጊነቱ በባህላዊ የዳታ ማቅረቢያ ሸክላ (ሻቲያ) እየተደረገ ለምግብነት ይውላል።

በተመስገን ተስፋዬ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top