ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ በአፍሪካ የቱሪዝም አብዮት ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወቱ የሚገኙ ሀገራት ሆነዋል።
ወደ አህጉሪቱ የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር ላይ አስደናቂ ጭማሪ እየታየ ነው ነው። እነዚህ ሀገራት ልዩ የሆኑ የባህል ልምዶችን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን፣ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶችንና ዓለም አቀፍ የገበያ ስትራቴጂዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ኢንቨስት እያደረጉ ነው።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በሄደው የቱሪዝም ዘርፍ እነዚህ ሀገራት በበለጸጉ ታሪኮቻቸው፣ ሳቢ በመሆነው የመሬት አቀማመጣቸው እና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን በጠበቁ የተለያዩ አገልግሎቶች ምክንያት ትኩረትን እየሳቡ ነው።
እ.አ.አ. በ2023 ብቻ ዘጠኝ ዋና ዋና የአፍሪካ ሀገራት በአጠቃላይ ከ50 ሚሊዮን በላይ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን ተቀብለዋል። ይህም የአህጉሪቱ ተወዳጅነት እያደገ መምጣቱን በግልጽ የሚያሳይ ነው።
ለአፍሪካ የቱሪዝም ዕድገት በጎ ተጽዕኖ ያላቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
የታላላቅ ስፖርታዊ ዝግጅቶች ሚና
በአፍሪካ የተዘጋጁ ታላላቅ የስፖርት መድረኮች ቁጥር መጨመር ለቱሪዝም መነቃቃቱ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ከሆኑት ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው።
ከቀጣይ ውድድሮች ጋር በተያያዘም የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ ይገኛል።
ለአብነት ሞሮኮ የ2030 የፊፋ የዓለም ዋንጫ ውድድርን ከስፔንና ከፖርቹጋል ጋር በጋራ ለማዘጋጀት እየተሰናዳች ይገኛል።
በተጨማሪም ደቡብ አፍሪካ እና ሩዋንዳ በሚቀጥሉት ዓመታት በፎርሙላ 1 የውድድር መርሃ ግብር ላይ ቦታ ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ሲሆን፣ ይህም አፍሪካን በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ ላይ ይበልጥ ትኩረት እንድታገኝ ያደርጋል።
እንደነዚህ ያሉ ዝግጅቶችን ተከትሎ የሚመጣው ዓለም አቀፍ ትኩረት፣ ለጨዋታዎቹ የሚጎርፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደጋፊዎች እና ተያያዥ ክንውኖች ቱሪዝሙን ያሳድጋሉ።
መጠነ ሰፊ ዝግጅቶቹ አፍሪካ የጉዞ መዳረሻ መሆኗን በተመለከተ ግንዛቤን ከማሳደግ ባለፈ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ግንባታንም እያመጡ ነው።
ዓለም አቀፍ ብራንዶች በቱሪዝሙ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ
ከቱሪዝም ዕድገት ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ ሆቴሎችና የቅንጦት ብራንዶች የአፍሪካን ገበያ እያማተሩ ይገኛል።
ከዓለም ትላልቅ ሆቴል አንዱ የሆነው ማርዮት እንደ ኬፕ ቨርዴ፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ያሉ መዳረሻዎችን ጨምሮ በ20 የአፍሪካ ሀገራት 130 ቅርንጫፎችን ከፍቷል። ይህ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የሚኖረው በጎ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም።
ሆኖም አንዳንደ ጊዜ ችገሮች ማጋጠማቸው አልቀረም። በተለይ ማርዮት በኬንያ ማሳይ ማራ ብሔራዊ ፓርክ ሆቴል በመክፈቱ ተቃውሞ ገጥሞታል። ይህ እርምጃ ተፈጥን እና የአካባቢውን ባህል ሊጎዳ እንደሚችል ተቺዎች ይከራከራሉ።
ቢሆንም የዓለም አቀፍ ብራንዶች ወደአህጉሪቷ መጉረፋቸው የቱሪዝም መሰረተ ልማቱን ለማዘመን ይረዳል።
አፍሪካ በአዋጭ የጉዞ ፓኬጆች
ለብዙ ዓመታት ወደአፍሪካ የሚደረግ ጉዞ ከከፍተኛ ወጪ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ለሀብታሞችና ከፍተኛ ትርፍ ገቢ ላላቸው ሰዎች ብቻ የተወሰነ ነበር። ሆኖም ግን ይህ ገጽታ በፍጥነት እየተለወጠ ነው።
ዛሬ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ወጣትና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ተጓዦች በተለይም ለዕረፍት ወደ አፍሪካ እየጎረፉ ነው።
ይህ ለውጥ የመጣው በዓለም አቀፍ የአየር ጉዞ መሻሻሎችና ሰፊውን የህብረተሰብ ክፍል የሚያስተናግዱ ይበልጥ ወጪ ቆጣቢ የጉዞ ፓኬጆች በመኖራቸው ነው።
ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው የጉብኝት አማራጮችና የፓኬጅ ስምምነቶች በመበራከታቸው፣ አፍሪካ ጀብዱ የተሞላበት ጉብኝት ለሚፈልጉና በጀታቸውን ለሚያገናዝቡ ተጓዦች ማራኪ መዳረሻ እየሆነች ነው።
ማኅበራዊ ሚዲያው በአመለካከት ለውጥ ላይ ያለው ኃይል
እንደ ኢንስታግራም እና ቲክቶክ ያሉ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች መበራከት አፍሪካ ለውጭው ዓለም በምትገለጽበት መንገድ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።
ማህበራዊ ሚዲያዎቹ ተጓዦች እንደ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና አልጄሪያ ያሉ ቦታዎችን በተመለከተ የእውነተኛ ጊዜ ልምዶቻቸውን እንዲያጋሩ ዕድል ፈጥረዋል።
እነዚህ ጊዜ ያለፈባቸውን አመለካከቶች በመሞገት የአህጉሪቱን የባህል ብልጽግና እና የተፈጥሮ ውበት ያሳያሉ። በዚህም የተነሳ፣ ብዙ ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የአህጉሪቱን ዕምቅ የቱሪዝም ሃብቶች እየጎበኙ በመሆናቸው ወደ አፍሪካ ለመጓዝ ያለው ፍላጎት እያደገ ነው።
የባህር ዳርቻ የሽርሽር ጉዞዎች መበራከት
ከ30 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሚዘረጋው የአፍሪካ አስደማሚ የባህር ዳርቻ ቱሪስቶችን ወደ አህጉሪቱ ከሚስቡ ቁልፍ ምክንያቶች አንዱ ነው።
ከቅርብ ዓመታት የታየው የባህር ዳርቻ የሽርሽር ጉዞዎች ዕድገት ተጓዦች አህጉሪቱን የሚቃኙባቸውን አዳዲስ መንገዶች ከፍቷል። ቱሪስቶች አሁን ላይ የአህጉሪቱን ደሴቶች፣ የአሳ አጥማጆች መንደሮችና ንጹህ የባህር ዳርቻዎችን ውበት የማየት ዕድል አግኝተዋል።