የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል የለውጥ ፍኖተ ካርታ ከ3 ዓመት በፊት ተግባራዊ መደረጉ ይታወሳል፡፡
ይህንን ተከትሎም የባህላዊ ፍርድ ቤቶች በስፋት ተቋቁመው ስራ መጀመራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የአዲስ ቀን የዜና ሾው ይህንን የሃገር ጉዳይ አስመልክቶ እንግዶችን በስቱዲዮ ጋብዞ አነጋግሯል፡፡
በፍትህ ሚኒስቴር የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ እና የለውጥ ስራ አመራር የሆኑት አቶ ኖህ ታከለ፤ ዘመናዊ የሆነ የህግ ስርዓት ከመምጣቱ በፊት የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ግጭቶቻቸውን በራሳቸው ባህላዊ በሆነ መንገድ ይፈቱ ነበር ብለዋል፡፡
የ3 ዓመቱ የለውጥ ፍኖተ ካርታ ደግሞ የባህላዊ የዳኝነት ስርዓት እንዲጠናከር ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
ይህ አሰራር በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ ለማድረግ ጥናቶችን በመስራት ጥንካሬ እና ድክመቶችን ለይቶ ሞዴል የሚሆኑ የህግ ስርዓቶችን በማዘጋጀት ለክልሎች ማሰራጨት እንደተቻለም ጠቅሰዋል፡፡
አያይዘውም በዚህ ሞዴል መሰረት ክልሎችም የራሳቸውን ህግ በራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ በማዘጋጀት ለማውጣት ጥረት አድርገዋል ነው ያሉት፡፡
ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት መደበኛውን የፍትህ ስርዓት እየደገፈ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ አንዱን አሸናፊ አንዱን ተሸናፊ የሚያደርግ አሰራር አለመሆኑንም አንስተዋል፡፡
ባህላዊ የሆኑ የፍትህ አሰጣጥ ስርዓቶችን እውቅና በመስጠት ማህበረሰቡ ግጭቶችን በባሕሉ መሰረት እንዲፈታ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነገሮችን ማስቀጠል እንዲቻል ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
የፍትህ ስርዓቱን በቋሚነት ለማሻሻል የለውጥ ፍኖተ ካርታ ውስጥ የተካተቱ እቅዶች በመሰረታዊነት የፍትህ ስርዓቱን ያሻሽላሉ፤ የማህበረሰቡን ቅሬታ ይፈታሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም አቶ ኖህ ተናግረዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሩ በበኩላቸው፤ የፍትህ ስርዓቱ የለውጥ ፍኖተ ካርታውን በትክክል በመተግበር ፍርድ ቤት ላይ እየመጡ ያሉ ውጤቶች እጅግ አበረታች ናቸው ብለዋል፡፡
በተያያዘም የባለጉዳይን እንግልት ለማስቀረት በቴክኖሎጂ አማኝነት ክልሎችም ተሞክሮ በመውሰድ እየተሰራ ያለው ስራ የሚበረታታ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ