ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለአሜሪካ ጸጥታ ስጋት ናቸው ያሏቸውን 12 ሀገራት በመጥቀስ፤ ከነዚህ ሀገራት ወደ አሜሪካ የሚደረገውን ጉዞ የሚከለክል አዋጅ ትንናት አመሻሽ ላይ ፈርመዋል።
እገዳው ከ 12 አገሮች የመጡ ዜጎችን ሙሉ በሙሉ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያደርግ ሲሆን፤ አፍጋኒስታን፣ ሚያንማር፣ ቻድ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኤርትራ፣ ሄይቲ፣ ኢራን፣ ሊቢያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ እና የመን እገዳው የተጣለባቸው ሀገራት ሆነዋል።
ከዚህም ባለፈ ብሩንዲ፣ ኩባ፣ ላኦስ፣ ሴራሊዮን፣ ቶጎ፣ ቱርክሜኒስታን እና ቬንዙዌላ ከፊል እገዳ የተጣለባቸው ሀገራት ሆነዋል።
እገዳው ሕጋዊ ለሆኑ ቋሚ ነዋሪዎች፣ ነባር ቪዛ ለያዙ፣ ለተለዩ የቪዛ ምድቦች እንዲሁም የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ ግለሰቦችን አያካትትም ተብሏል።
አንድ የዋይት ሀውስ ባለስልጣን፥ ፕሬዚዳንቱ አስቀድመው አዋጁን ለመፈረም ሲያስቡ እንደነበር ጠቅሰው በቦልደር ኮሎራዶ የተፈጸመውን ፀረ-ሴማዊ ጥቃት ተከትሎ አዋጁን በፍጥነት ፈርመዋል ሲሉ ለሲኤንኤን ተናግረዋል።
የዋይት ሀውስ ምክትል ፕሬስ ሴክሬታሪ አቢጌል ጃክሰን በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት "ፕሬዚዳንት ትራምፕ የአሜሪካን ዜጎች ወደ አገሪቱ ከሚገቡ አደገኛ የውጭ ተዋናዮች ለመጠበቅ የገቡትን ቃል እየፈጸሙ ነው" ሲሉ ጽፈዋል።
በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ትራምፕ ሰባት የሙስሊም ሀገራት ተጓዦች ወደ አሜሪካ እንዳይመጡ መከልከላቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ይህን ፖሊሲ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስልጣን ሲይዙ ሽረውት ነበር።