ከሻምፒዮንነት እስከ መውረድ ስጋት ፋሲል ከነማ

6 Days Ago 231
ከሻምፒዮንነት እስከ መውረድ ስጋት  ፋሲል ከነማ

ወደ ሀገሪቱ ትልቁ ሊግ ያደገው በ2009 ዓ.ም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ከተቀላቀሉ በኋላ በአጭር ጊዜ ጠንከራ ተፎካካሪ ከመሆን አልፈው ዋንጫ ካነሱት ጥቂት ክለቦችም ቀዳሚው ነው፡፡

በሊጉ መሳተፍ ከጀመረበት 2000ዎቹ መጨረሻ እስከ አሁን ድረስ ባሉት አመታት በሀገሪቱ እግር ኳስ ላይ ትልቅ መነቃቃት ፈጥሯል፡፡

በተለይ ለአመታት የአዲስ አበባ ከተማ ክለቦች በበዙበት እና ጥቂት የሚባሉ የክልል ክለቦች ብቻ በነበሩበት ጊዜ እንደ ፋሲል ከነማ አይነት ጠንካራ ቡደኖች መምጣታቸው የሊጉን የፉክክር ደረጃ ከፍ አድርጎታል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከሱፐር ሰፖርት መምጣት በፊት የፕሪሚየር ሊግ  ጨዋታዎች እንደ አሁኑ በተመረጡ ከተሞች ብቻ ሳይሆን በሁሉም የክልል ከተሞች በሚደረጉበት በዚያ ጊዜ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች  በሁሉም ቦታዎች እየተዘዋወሩ ቡድናቸውን የሚደግፉበት መንገድ  ያለ ደጋፊ ሙሉ ለማይሆነው እግር ኳስ ሌላ ውበት ሰጥቶታል፡፡

ለረጅም ጊዜ በፕሪሚየር ሊግ  የሚሳትፈው ክለብ ያልነበረው አማራ ክልል የዳሽን ቢራ እና ወልድያ ከተማ ወደ ሊጉ መምጣት በክልሉ እግር ኳስ ላይ ትልቅ መነቃቃት ሲፈጥር የፋሲል ከነማ እና የባህር ዳር ከተማ ተሳትፎ ደግሞ እግር ኳሱ ይበልጥ በተደረጃ መልኩ ከመዝናኛነት በላፈ ሀብት እንዲሆንም በር ከፍቷል።

ባለፉት አመታት ብዙ ክለቦች ሊጉን መቋቋም ተስኗቸው በመጡበት ሲመለሱ ፋሲል ከነማ ግን የሊጉ ድምቀትም ተፎካካሪም ሆኖ ቆይቷል።

በሊጉ የመጀመርያ ተሳትፎው 2009 ዓ.ም  6ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ክለቡ ባለፉት ስምንት አመታት ዝቅተኛ ውጤቱ 7ኛ ደረጃን ይዞ የጨረሰበት ነው። ፋሲል ከነማ ከከፍተኛ ሊግ ባደገ በ3ኛው አመት በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመራ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ለማንሳት እስከ መጨረሻው 30ኛ ሳምንት ተፎካክሮ ክብሩን በመቐለ ሰባ እንደርታ የተነጠቀበት በደጋፊዎች ዘንድ የሚረሳ አልነበረም።

ቢሆንም ግን በዚያኑ አመት የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ያነሳው ፋሲል ከነማ ለመጀመርያ ጊዜ በአፍሪካ መድረክ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን የወከለበት ነበር።

ክለቡ በቀጣዩ አመት በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ እየተመራ በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ቢቀርብም ውድድሩ በኮቪድ ምክንያት ከ12ኛ ሳምንት በላይ መጓዝ ባለመቻሉ ሌላ አመት ለመጠበቅ ተገዷል።

2013 ዓ.ም ለፋሲል ከነማ የተለየ የውድድር አመት ነው። በአሳማኝ ብቃት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ያነሳበት ደግሞም በአፍሪካ ትልቁ የክለቦች ውድድር በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ መሳተፉን ያረጋገጠበት።

ፋሲል በ2014ም  ቢሆን እስከ መጨረሻው ሳምንት ለሊጉ ክብር የተፎካከረበት ነው። ምንም እንኳን በ30ኛ ሳምንት መርሀ ግብር የራሱን ዕድል በራሱ የሚወስነው ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አበባ ከተማን አሸንፎ ዋንጫውን ማንሳቱን ቢያረጋግጥም።

አንድ ጊዜ የጥሎ ማለፍ አንድ ጊዜ ደግሞ የሊጉን ክብር ያነሳው ክለብ በዚህ አመት ላለመውረድ እየተጫወተ ይገኛል።

ሊጠናቀቅ የ3 ጨዋታ እድሜ ብቻ በቀረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በውበቱ አባተ የሚመራው ቡድን በ38 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ካደረጋቸው 31 ጨዋታዎች ስምንቱን ብቻ  ያሸነፈው ፋሲል  ዛሬ በ34ኛ ሳምንት በእኩል ነጥብ በደረጃ ሰንጠረጁ 13ኛ ላይ ከሚገኝው እና የመውረድ ስጋት ካለበት ኢትዮ ኤሌክትሪክ  ወሳኝ ጨዋተውን ያደርጋል።  ዛሬ 12 ሰዓት ላይ የሚደረገው ጨዋታ ሁለት የመትረፍ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ የሚታገሉ ቡድኖች የሚገናኙበት በመሆኑ በትልቁ ይጠበቃል።

አራት ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ በሚወርዱበት አመት ፋሲል ከነማ  በሊጉ ለመቆየት የዛሬውን ጨምሮ ከቀሩት 3 ጨዋታዎች  ነጥቦችን መሰብሰብ ይጠበቅበታል።

በተለይ  በ35ኛ ሳምንት መርሀ ግብር  ከሌላኛው የመውረድ አደጋ ከተጋረጠበት አዳማ ከተማ የሚያደርገው ጨዋታ የጥሎ ማለፍ ያክል ወሳኝ ይሆናል።

በአንተነህ ሲሳይ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top