ትዕይንተ ሕዝብ የታሪኳ አካል የሆነው ሎስ አንጀለስ

4 Days Ago 1386
ትዕይንተ ሕዝብ የታሪኳ አካል የሆነው ሎስ አንጀለስ

የአሜሪካ መንግሥት ሰነድ አልባ ስደተኞችን መያዝ መጀመሩን ተከትሎ ከአምስት ቀናት በፊት የተጀመረው የሎስ አንጀለስ ተቃውሞ ዛሬም ተቀጣጥሎ ቀጥሏል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተቃውሞው ከአካባቢው የፖሊስ ኃይል አቅም በላይ መሆኑን ጠቅሰው ብሔራዊ ዘብ ወደ ከተማዋ እንዲገባ ያደረጉት በመጀመሪያዎቹ ቀናት ሲሆን፣ ተቃውሞው ግን ከመብረድ ይልቅ እየተባባሰ ቀጥሏል።

ፖሊሶች ሕዝቡን ለመበተን ውኃ እና አስለቃሽ ጋዝ እየተጠቀሙ ሲሆን፣ ለዚህም በርካታ ሰው አልባ ተሸከርካሪዎች በሥራ ላይ ውለዋል። በከተማዋም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።

የፌዴራል መንግሥት ንብረቶችን ለመጠበቅ በሚል በመጀመሪያ ዙር ወደ 300 የሚጠጉ የብሔራዊ ዘብ አባላት ወደ ከተማዋ ገብተዋል። ፕሬዚዳንቱ ያለ ግዛቲቱ አስተዳደር ጥያቄ ወይም ፈቃድ ብሔራዊ ዘብ እንዲገባ ሲያዝዙ በአሥርት ዓመታት ውስጥ ይህ የመጀመሪያ እንደሆነ ነው የተነገረው። 

ባለፈው ወደ አካባቢው ከተንቀሳቀሱት 500 በላይ የብሔራዊ ዘብ አባላት በተጨማሪ በትናንትናው ዕለት ወደ 700 የሚጠጉ የባሕር ኃይል ሠራተኞች በዛሬው ዕለት ወደ አካባቢው ገብተዋል። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተጨማሪ የብሔራዊ ዘብ አባላት እንዲንቀሳቀሱም ትዕዛዝ ሰጥዋል። 

የካሊፎርኒያ አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሶም እና የሎስ አንጀለስ ከንቲባ ካረን ባስ የፌዴራሉን መንግሥት እርምጃ ያጣጣሉ ሲሆን፣ ከንቲባው “የፌዴራል መንግሥት ከተማዋን ቤተ ሙከራ እያደረጋት ነው” ሲሉ ከስሰዋል።

ተቃውሞው እየተባባሰ በመምጣቱ በዛሬው ዕለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በከተማዋ ታውጇል። አዋጁ ከምሽቱ 2:00 ሰዓት እስከ ሌሊቱ 6:00 ሰዓት ያለውን የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚገድብ ሲሆን፣ የከተማዋ ከንቲባ ካረን ባስ አዋጁን ጥሶ የተገኘ ሰው እንደሚያዝ አስጠንቅቀዋል።

ሎስ አንጀለስ እና ትዕይንተ ሕዝብ

ሎስ አንጀለስ በደቡብ ካሊፎርኒያ የምትገኝ እና የሀገሪቱ የፊልም እና የቴሌቪዥን ኢንዱስትሪ በዙሪያዋ የሚገኙባት ከተማ ነች። ከተማዋ ሆሊውድን ጨምሮ "Paramount Pictures፣ Universal and Warner Brothers" በተባሉ የቪዲዮ እና ቴሌቪዥን ስቱዲዎች የተከበበች ነች። 

ይህች ከተማ በተለያዩ ወቅቶች የተቃውሞ ሰልፎችን በማድረግ ከአሜሪካ ከተሞች ከዋሽንግተን ዲሲ ቀጥላ ሁለተኛውን ስፍራ እንደምትይዝ የዘጋርዲያን መረጃ ያመላክታል።

በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ብቻ በርካታ ተቃውሞችን በማስተናገድ የምትታወቅ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ደግሞ የስደተኞች መብት ጥበቃን እና የጥቁሮችን መብት አስመልክቶ የተደረጉት ተቃውሞዎች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።

እ.አ.አ. በ2006 የስደተኞችን መብት አስመልክቶ በከተማው የተደረገው ታላቅ ተቃውሞ አንዱ ነበር። በሺህዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች የተሳተፉበት ይህ ሰልፍ፣ “ሰነድ አልባ ስደተኞች ወንጀል እየፈፀሙ ነው” በሚል ሊወጣ የነበረውን ሕግ ለመቃወም ያለመ ነበር። ሕጉ ስደተኞቹን ብቻ ሳይሆን እነርሱን የሚረዱትን ተጠያቂ ያደርጋል መባሉ ደገሞ ተቃውሞውን ያባባሰ ነበር። በመጨረሻም ሴኔቱ የሕጉን ሐገረጎች በማለዘብ እና በወንጀል ተጠያቂ ያልሆኑ ስደተኞች ዜግነት የሚያገኙበት የሕግ አንቀፅ በማካተቱ ተቃሞው ለዝቧል።

እ.አ.አ ነሐሴ 9 ቀን 2014 የ18 ዓመቱ ጥቁር ወጣት ማይክል ብራውን ጁኒየር በሚዙሪ ነጭ ፖሊስ መኮንን በጥይት ተገደለ። የዚህ ወጣት መገደል በሎስ አንጀለስ ከፍተኛ ተቃውሞ እና ብጥብጥ እንዲከሰት ያደረገ ሲሆን፣ ፖሊስ በጥቁሮች ላይ እየፈጸመ ነው ያሉትን የኃይል አጠቃቀም እና ጭካኔ አውግዘዋል። ፍርድ ቤት ዊልሰን የተባለውን ነጭ ፖሊስ በነፃ መልቀቁ ደግሞ በከተማዋ ውስጥ ሌላ አለመረጋጋት እንዲከሰት አድርጎ ነበር።

በ2017 የሴቶች መብት ተማልቶ ይከበር (Women's Marches) በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስተው ነበር። በወቅቱ በነቂስ በመውጣት ሴቶች በሁለንተናዊ መልኩ መብታቸው እንዲከበር የጠየቁት የከተማዋ ነዋሪዎች ዛሬም ይህን ጥያቄ አላቋረጡም። በዚህ ተቃውሞ ላይ ከ750 በላይ ሰዎች መሳተፋቸው ደግሞ በከተማዋ ታሪክ ታላቅ የተቃውሞ ትዕይንተ ሕዝብ ሆኖ እንዲመዘገብ አድርጎታል።

በ2020 በነጭ ፖሊስ ታፍኖ የተገደለውን ጆርጅ ፍሎይድን ሞት ተከሎም በመላው አሜሪካ ተቃውሞ እንደነበር ይታወሳል። ሎስ አንጀለስ ግን ከሁሉም የአሜሪካ ከተሞች በተለየ ሁኔታ ተቃውሞን አቀጣጥላ እስከ አሁን ጆርጅ ፎሎይድን እያሰበች ትገኛለች። የከተማዋ ነዋሪዎች ባገኙት አጋጣሚዎች ሁሉ ለጆርጅ ፍሎይድ እና መሰል ሰዎች የፍትሕ ያለህ ድምፃቸውን እንዳሰሙ ናቸው።

ሎስ አንጀለስ በአየር ንብረት ለውጥ የተቃውሞ እንቅስቃሴም የምትታወቅ ከተማ ነች። በተለይም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት መውጣታቸውን ሲያስታውቁ ከሎስ አንጀለስ በላይ ድምፅ ያሰማ ከተማ አልነበረም። ስለ አካባቢያዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ግንዛቤ አላቸው የሚባሉት የሎስ አንጀለስ ነዋሪዎች ጠንካራ የአካባቢ ፖሊሲዎችን እና ዘላቂ ልምምዶች እንዲኖር ጠንካራ አቋሞችን አራምደዋል። ይህ በአብዛኛው ወጣቶች የሚሳተፉበት የአየር ንብረት ለውጥ ተቃውሞ በየዓመቱ የሚደረግ እንደሆነ የዋሽንግተን ፖስት መረጃ ያመላክታል።

በፍልስጤም ጉዳይም ከሎስ አንጀለስ በላይ ተቃውሞ ያሰማ አካባቢ የለም። አሜሪካ በፍልስጤማውያን አንጻር ትከተላለች ያሉትን የተዛባ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንድታስካክል ደጋግመው ጠይቀዋል። እስራኤል ፍልስጤማውያን ላይ የምታደርሰውን ግፍ ሀገራቸው እንድታወግዝም ሲጠይቁ ከፖሊሶች ጋር ተጋጭተዋል።

በታሪኳ በትዕይንተ ሕዝብ ተቃውሞ በማሰማት የምትታወቀው ሎስ አንጀለስ ይኸው ዘንድሮም ስደተኞች በሥርዓት መያዝ አለባቸው ስትል ስደተኛ ጠል ናቸው የሚባሉትን የዶናልድ ትራምፕን አስተዳደር እየተሟገተች ታገኛለች።

ሎስ አንጀለስ ከ2000ዎቹ በፊትም በ1991 በነጭ ፖሊሶች በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለውን ሮድኒ ኪንግ ፍትሕ እንዲያገኝ ጠይቃለች። ከ1960ዎቹ መገባደጃ እስከ 1970ዎቹ አሜሪካ በቬትናም ላይ ያደረገችውን ጦርነት እና በትውልደ ሜከክስኮ አሜሪካውያን ላይ የሚደረገውን አድልኦ ለማውገዝ "Chicano Moratorium" የሚል ታቃውሞ አካሄዳለች። በመጋቢት 1968 በምሥራቅ ሎስ አንጀለስ የሚትገኘው ቺካኖ የሚገኙ ተማሪዎች በትምህርት ዕድል አድልኦን በመቃወም የተማሪዎች ተቃውሞ አድርጋለች።

የሎስ አንጀለስ የተቃውሞ ታሪክ ቀጣይ የሆነ ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲኖር፣ ሕዝባዊ መብቶች በቁርጠኝነት እንዲከበሩ፣ እንዲሁም እኩልነት እና የፍትሕ በከተማዋ እና በአሜሪካ እዲሰፍን የሚደረገው ትግል ማሳያ እንደሆነ በርካቶች ይናገራሉ።

ሮይተርስ ከ2023 እስከ 2024 ያለውን መረጃ ጠቅሶ እንዳሰፈረው፣ በሎስ አንጀለስ 48.6 በመቶ ሂስፓኒክ ወይም ላቲኖ፣ 24.55 በመቶ ላቲኖ ያልሆኑ ነጭጮች፣ 15.1 በመቶ የእስያ ዝርያ ያላቸው ማኅበረሰቦች፣ 7.3 በመቶ ጥቁሮች፣ 0.2 በመቶ የቀድሞ የአሜሪካ ተወላጆች፣ 3.5 ከመቶ ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ይኖራሉ። የመረጃ ምንጮቻችን ሮይተርስ፣ ሲኤን ኤን፣ ኢሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ናቸው።

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top