የነብዩላሂ ኢብራሂም የፈጣሪ ፍቅር፤ የኢስማኤል ታዛዥነት በአረፋ ተራራ ተፈትኖ አለፈ

13 Hrs Ago 112
የነብዩላሂ ኢብራሂም የፈጣሪ ፍቅር፤ የኢስማኤል ታዛዥነት በአረፋ ተራራ ተፈትኖ አለፈ
ነብዩላሂ ኢብራሂም ከአሏህ ነብያቶችና መልዕክተኞች መካከል አንዱ ናቸው። የትልቅ ስብዕና ባለቤት ሲሆኑ በሁሉም አጋጣሚ እና ሁኔታ አሏህን ፈሪም ነበሩ። ከጣኦት አምላኪ ቤተሰብ የወጡት ነብዩላሂ ኢብራሂም ገና በልጅነታቸው ነበር የሰው አለማስተዋል የተገነዘቡት።
የሚገርመው የኢብራሂም አባት ነበሩ ለከተማይቱ ህዝብ የተለያዩ ጣኦታትን እየሰሩ የሚሸጡላቸው። ነብዩላሂ ኢብራሂም በጣም ማሰላሰል እና ማገናዘብ ሲጀምሩ እንዴት አባቴ ከእንጨት እና ከድንጋይ እየጠረበ የሚሸጠውን ግዑዝ ነገር ሰው ያመልከዋል በማለት ትክክለኛውን አምላክ መፈለግ ጀመሩ። ትክክለኛውን አምላክ ፍለጋ ሲጀምሩ ጨረቃ፣ ፀሀይ፣ ኮከብ አምላክ ናቸው ብለው ሲወስኑ እነሱን የሚቆጣጠር አንድ አካል እንዳለ ተረዱ። ያ ጌታ ደሞ በአይን ሊታይ እንደማይችልም ተገንዝበው በዛ የፍጥረተ አለሙ ጌታው በሆነው አሏህ መሆኑን አመኑ።
ህዝቡንም ከዚህ አምልኮ ለማውጣት ሲሞክሩ ንጉሥ እና ህዝቡ ኢብራሂምን ለማቃጠል ተራራ የሚያክል አንጨት አቀጣጥለው ጣሏቸው አሳቸው በእሳቱ ላይ ለአርባ ቀን ቆይተው ሲወጡ ውበታቸው ሰባ እጥፍ ጨምሮ ነበር።
ነብዩላሂ ኢብራሂም ሚስታቸው ሳራ መሀን ስለነበረች ሳራ አገልጋያቸውን አግብተው ልጅ እንዲወልዱ ስትጠይቃቸው አይሆንም ቢሉም እሷ ግን አሳምነዋቸው ሀጃርን አገቡ።
ነብዩላሂ ኢብራሂም ሀጃር ከምትባል አጋራቸው የበኩር ልጃቸውን ኢስማኤልን ከወለዱ በኋላ፣ በቤታቸው እንዲቀመጡ በወቅቱ መካን የነበረችው ባለቤታቸው ሳራ ውስጧ አልፈቀደም ነበር፣ ታድያ በአንደኛው ቀን አላህ ለነቢዩላሂ ኢብራሂም ሀጀርና ኢስማኤልን ይዘው ወደ አረቢያ ምድር እንዲወጡ ነብዩ አዘዛቸው።
ነብዩላሂ ኢብራሂም የአላህን ቃል በመቀበል ምንም ምግብም ሆነ መጠጥ እንዲሁም መጠለያ ወደሌለው በረሀ አሁን ላይ መካ በመባል ወደምትታወቀ ቦታ ይዘዋቸው ይሄዳሉ እዛም እናት እና ልጁን ትተዋቸው ሄዱ።

ትንሹ ኢስማኤልም በውሃ ጥም የተነሳ ያለቅሳል፤ መሬቱንም በእግሩ ይመታ ነበር፤ ሀጃርም የምታደርገው ግራ ቢገባት ውሃ ፍለጋ ትሮጥ ጀመረች። መጀመርያም ወደ ሳፋ ተራራ ከዛም ወደ ማርዋህ ተራራ እየሮጠች ውሃ ትፈልግ ነበር፤ 7 ጊዜ ያህል እንደተመላለሰች ልጇ ኢስማኤል በእግሩ መሬቱን ሲመታ የነበረበት ቦታ ላይ ውሃ ፈለቀ ይህም እስከዛሬ እየፈሰሰ የሚገኘው ዘምዘም በመባል ይታወቃል። ከዚያ ከዕለታት አንድ ቀን ነብዩላሂ ኢብራሂም በህልማቸው ፈጣሪ ልጃቸው ኢስማኤልን እንዲሰውለት ሲጠይቃቸው ታያቸው፡፡
ይህም ህልም ሶስት ጊዜ ይታያቸዋል እሳቸውም ለጌታቸው ታዛዥ ስለነበሩ ወደ መካ አቀኑ በዚያም ሲደርሱም ለኢስማኤል ያዩትን ህልም እና ውሳኔያቸውን ነገሩት። ሸይጧን በብዙ ሊያሳስታቸው ቢፈልግም ኢስማኤል ታዛዥ ልጅ ስለነበር የፈጣሪ ፍላጎት ከሆነ ራሱን መሰዋዕት አድርጎ ለማቅረብ በሐሳባቸው ተስማማ፡፡ ኢስማኤል ወደ አባቱ ዘወር አለና “አባቴ ሆይ የታዘዝከውን ፈፅም በአላህ ፈቃድ ከታጋሾች ሁኜ ታገኘኛለህ።” አላቸው። ወደ አረፋ ተራራ አባት እና ልጅ ወጡ ነገር ግን ድርጊቱ ለነብዩላሂ ኢብራሂም ቀላል እንዳልነበረም ።

ሐሳባቸውን ቀይረው ሁለት ሦስት ጊዜያት ያህል ከተራራው ወርደው ነበር፤ ይሁንና የፈጣሪ ትዕዛዝ ከልጃቸው እንደማይበልጥ በማሰብ ቢላውን ከልጃቸው አንገት ላይ አሳረፉት ግን አልቻለም በዚህም ጊዜ አንድ ተአምር ተፈጠረ ከወደ ሰማይ ያልተጠበቀ ጥሪ ተሰማ፡፡ “ኢብራሂም… ኢብራሂም… ታላቅነትህን አስመስክረሃልና እርዱን አቆየው” ተባሉ፡፡ ድምፁ የመላእክተኛው ጅብሪል ነበር፡፡ በኢስማኤል ምትክም መልአኩ ያመጣውን በግ እንዲያርዱና ልጁን ወደቤቱ እንዲመልሱ ነገራቸው በኢስማኤል ምትክ ከሰማይ የወረደው በግ ታረደ፡፡
የነብዩላሂ ኢብራሂም የፈጣሪ ፍቅር፤ የኢስማኤል ታዛዥነት በአረፋ ተራራ ተፈትኖ አለፈ፡፡ ኢብራሂም እና ኢስማኤል ለፈጣሪያቸው ተገዥነታቸውን አስመስክረው በአሏህ ዘንድ ሞገስን አገኙ፡፡ አባት እና ልጅ ለፈጣሪ መታዘዝን በግልጽ ያሳዩባት ያቺ ዕለት የዒድ አል አድሐ በዓል ሆና እንድትከበርም ተወሰነ፡፡
መልካም በዓል
በቢታኒያ ሲሳይ
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top