ከቀናት ሁሉ ልዩ የሆኑት የዙልሂጃ የመጀመሪያ 10 ቀናት

15 Hrs Ago 103
ከቀናት ሁሉ ልዩ የሆኑት የዙልሂጃ የመጀመሪያ 10 ቀናት

ለእስልምና እምነት ተከታዮች ሁሉ የተሰጡ እና የመልካም ነገራቶች በር የሚከፈትባቸው፣ የኸይር አየር የሚነፍስባቸው፣ ሰው ሁሉ ወደ ነብሱ የሚቀርብባቸው ቀናት አሉ - የዙልሂጃ የመጀመሪያ አሥርቱ ቀናት።

በእስልምና አቆጣጠር የመጨረሻው የዙልሂጃ ወር 10 ቀናት የሆኑትን እነዚህን ቀናት ታዲያ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከቀናት ሁሉ በላጭ ናቸው ብለዋቸዋል። ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) "እነዚህን ቀናት ተገናኟቸው፣ ተጠቀሙባቸው" ያሉላቸው 10ቱ ቀናት እጅግ የሚወደደው እና ከእምነቱ መዓዘናት ውስጥ አንዱ የሆነው ሐጅ የሚደረግበት ወቅትም ናቸው።

በዓለም ላይ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞችም “አቤቱ ጌታችን ጥሪህን ተቀብለን መጣን” እያሉ ከአራቱም መዓዘናት ወደ መካ (በይቱላህ አል-ሀረም) ወደተከበረው የአላህ ቤት ይተምማሉ።

ቀናቱንም በፆም (በዒባዳ) እና በአምልኮ ማሳለፍ ትልቅ ምንዳ እንዳለው ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ተናግረዋል። በተለይ ዘጠኛዋን የዐረፋ ቀን በፆም ማሳለፍ ያለፈውን ዓመት እና የሚመጣውን ዓመት ወንጀል እንደሚያስምርም ይነገራል።

ሐጅ የሚያደርጉ ሰዎች ዘጠነኛዋን ቀን በዓረፋት ተራራ ላይ በመሆን ዕለቱን አላህን በማውሳት ዱአ በማድረግ ያሳልፋሉ። ቦታው ስያሜውን ያገኘው አደም እና ሐዋ ከገነት ከተባረሩ በኋላ የተገናኙበት ቦታ በመሆኑ ነው። በስፍራው ላይ ሆነውም “ዐረፍቱኪ /አረፍተኒ (አወቅሺኝ አወቅከኝ) ተባባሉ፤ ቦታውም 'ዓረፋት' ተብሎ ተሰየመ።

ለሐጅ ሥነ-ሥርዓት ዓረፋት ተራራ ላይ የሚወጣው እና የሚጸለየው በዚህ ዘጠነኛ ቀን ላይ በመሆኑ ቀኑ ዓረፋ እንደተባለ የሃይማኖቱ ክታቦች ያወሳሉ። በሌላ በኩል በእስልምና አቆጣጠር የመጨረሻው ወር የሆነው የዙልሂጃ 10ኛው ቀን በእስልምና ውስጥ ካሉ የተቀደሱ ቀናት አንዱ ነው።

እሱም የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል የሚከበርበት እና ‘የውም አል-ናህር' ወይም የእርድ ቀን ነው። ነብዩላሂ ኢብራሂም (ዐ.ሰ) ልጃቸውን ኢሳማኤልን “ሠዋልኝ” ብሎ አላህ ባዘዛቸው ጊዜ የጌታ ትዕዛዝ ነውና ለመሠዋት በወሰኑበት ጊዜም አላህ በእዝነቱ ከሰማይ ሙክት በግ አወረደላቸው።

ታዲያ ይሄን ታሪክ ለመዘከር በዚህ ዓረፋ በዓል ላይ እርድ ይከናወናል። ከዒድ ሶላት በኋላ የሚደረገው ይህ እርድም 'ኡዱሂያ' በመባል ይታወቃል። ከእርዱ የሚገኘውንም ሥጋ ሦስት ቦታ በመከፋፈል አንዱን ለራስ፣ ሌላኛውን ከቤተዘመድ ጋር፤ የቀረውን ደግሞ ለተቸገሩ ሰዎች በመስጠት የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን በአብሮነት ያሳልፋሉ።

በዚህ የእርድ ቀንም የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕዝበ ሙስሊሙ ዘንድ በድምቀት ይከበራል። የዙልሂጃ 10ቱ ቀናት ከመቸውም በበለጠ ሕዝበ ሙስሊሙ ነብሱን የሚክስበት፣ ደግ ነገር የሚያደርግበት፣ ከፈጣሪው ጋር በእጅጉ የሚቆራኝበት ቅዱስ ቀናት መሆናቸውን የሃይማኖቱ አባቶች ይገልጻሉ።

በሴራን ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top