በሺዎች የሚቆጠሩ የዓይን ህሙማን የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

19 Days Ago
በሺዎች የሚቆጠሩ የዓይን ህሙማን የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የአይን ህሙማን የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል የብራይት ጆርኒ ፕሮጀክት የመግባቢያ ሰነድ በጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣው ዢ ዩን መካከል ተፈርሟል፡፡

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ በኢትዮጵያ የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት ከተርሸሪ ህክምና በላይ ለማሳደግ መታቀዱን አስረድተዋል፡፡

ጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት በሃገሪቱ በማቅረብ ታካሚዎች ለህክምና ከሃገር በመውጣት የሚደርስባቸውን መጉላላት ለማስቀረት እየሰራ መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቀስው፤ ለዚህም ግብ መሳካት ከቻይና ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

አምባሳደር ዣው ዢ ዩን በበኩላቸው፤ የቻይና መንግስት ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ ዙር 21 ሺ ዶዝ የኮሌራ ክትባት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ ክትባቱ በተለይም ህጻናትን በኮሌራ ከመያዝ እንደሚከላከል አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የቻይና መንግስት በኢትዮጵያ ተጨማሪ ሶስት የህክምና ማእከሎችን ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆኑን አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የቻይና መንግስት በሃገር ውስጥ የህክምና ግብአቶችን የማምረት ተሞክሮውን ለኢትዮጵያ በማጋራት የኢትዮጵያን የህክምና ግብአቶችን እና መድሃኒቶችን በሃገር ውስጥ የማምረት ግብ እንዲሳካ እንዲሁም ቻይና በኢትዮጵያ የህክምና ዘርፍ ላይ የምታደርገው ኢንቨስትመንት ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር መደረጉን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top