Search

በሳዑዲ አረቢያ ኢ_ሰብዓዊ ድርጊት የተፈጸመባት መካ መሀመድ የሞራል ካሳ አገኘች፡- የሳዑዲ ኢምባሲ

ከ4 ወር በፊት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሪያድ ለሥራ ያቀናችው መካ መሀመድ አረጋው ለሁለት ዓመታት የሚያቆያትን ኮንትራት ተስማምታ ነበር፡፡

በሳዑዲ 4 ወራት ከሰራች በኋላ ወደ ቤተሰቧ እንዲመልሷት አሰሪዎቿን ብትጠይቅም አሰሪዎች ግን አሻፈረኝ በማለታቸው ይህ አለመግባባት እየሰፋ  በመሄዱ ወደ አልታወቀ ስፍራ ሊወስዷት እየጎተቱ ሲያንገላቷት መካ መሀመድ የድረሱልኝ ጩሀት ታሰማለች፡፡

በዚህም ሁለት ሴቶች እየጎተቷት ወደ መኪና ለማስገባት ትግል ሲያደርጉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማኅበራዊ ሚዲያ ተሰራጭቶ በርካቶችን አስቆጥቷል፡፡

ጉዳዮን የተመለከተው በሳዑዲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሰዎቹን ና የመኪናውን ታርጋ የያዘ ምስል በማዘጋጀት፣ የክስ ማመልከቻ አዘጋጅቶ ለሳዑዲ አረቢያ የጸጥታ አካላት ማስገባቱን በኢትዮጵያ ኢምባሲ የቆንስላ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ተማም አሊይ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግረዋል፡፡

ኤምባሲው ያቀረበውን ክስ መሰረት አድርጎ የሳዑዲ አረቢያ የጸጥታ አካላት ክትትል በማድረግ ሁለቱን ሴቶች በቁጥጥር ሥር በማዋል ተበዳይ መካ መሀመድን ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ኢምባሲ ቅጥር ጊቢ እንድትመለስ ማድረግ ችሏል፡፡

በሂደቱም የመካ መሀመድ አሰሪዎች የፈጸሙትን ኢ-ሰብዓዊ ተግባር በማመናቸው እና በመፅፅታቸው በቤተሰብ ደረጃ በድርድር እንዲያልቅ ለኢምባሲው ተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

መካ መሀመድ ጉዳዩ በሽምግልና እንዲያልቅ ተጠይቃ በመፍቀዷ 20 ሺህ የሳዑዲ ሪያል የሞራል ካሳ እንዲከፈላት በማድረግ እርቅ ማውረድ መቻሉን ኃላፊው አቶ ማም አሊይ ጎዱ ተናረግረዋል፡፡

መካ መሀመድ አረጋው አሁን ትኬት ተቆርጦላት ወደ አገር ቤት ቤተሰቦቿ ጋር እንድትመለስ እንደሚደረግ ኢምባሲው ገልጿል፡፡

አዲስ የወጣው የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ በሁለቱም  ወገኖች መብትና ግዴታቸውን ግልጽ በሆነ መልኩ ስለሚያስቀምጥ የሰራተኛውን መብትና ጥቅም ለማስከበር ምቹ ዕድል በመፍጠሩ በህጋዊ መንገድ የሄዱ ሰራተኞችን ደኅንነት ለመከታተል አጋዥ ሆኗል ብለዋል፡፡

በእንደዚህ አይነት መንገድ ዜጎች ለሥራ ወደውጭ ሃገር ሲሄዱ የሰራተኛውን  ሙሉ አድርሻ ኢምባሲው ጋር ስለሚደርስ ለክትትልና ለአሰራር ምቹ አድርጎታል ብለዋል፡፡

 

 

በመሀመድ ፊጣሞ