Search

የቻይናው ዥኑዋ ስለ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ምን አለ?

ኢትዮጵያ ከሥድስት ዓመታት በፊት የጀመረችው አረንጓዴ ዐሻራ ኢንሼቲቭ የተፈጥሮ ሥነ-ምህዳር መልሶ እንዲያገግም በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥ ንቅናቄን እየደገፈ እንደሚገኝ የቻይናው ዜና ወኪሊ ዥኑዋ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ በከባድ የአየር ንብረት ለውጥ እየተጎዳች ያለች ሀገር መሆኗን የሚጠቅሰው ዥኑዋ፣ የአካባቢ ሥነ ምህዳርን መልሶ እንዲያገግም ማድረግ ለችግሩ መፍትሔ መሆኑን አምና አረንጓዴ ዐሻራን እንደጀመረች ይገልጻል።

የአየር ንብረት ለውጥ አካባቢን እያራቆተ የምግብ ዋስትና ላይ ፈተና መደቀኑን ያስዋለችው ኢትዮጵያ፣ በመፍትሔው ላይ አተኩራ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን ቀርጻ ወደ ሥራ መግባቷ ተጠቅሷል።

የዚህን ዓመት መርሐ ግብር መጀመሯን እና በክረምቱ ወራት 7.5 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል መርሐ ግብሩ ከተጀመረ አንስቶ የተተከሉትን ችግኞች ቁጥር 47.5 ቢሊዮን ዛፎች በላይ ለማድረስ እየሠራች እንደምትገኝ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራን ውጤታማ ለማድረግ የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ ለማልማት የሚውል ልዩ ፈንድ የሚደነግግ አዋጅ በፓርላማው ማጽደቋም ጠቅሷል።

አዋጁ በደን ልማት የተራቆተን መሬት መልሶ አረንጓዴ ለማልበስ ከፌደራል መንግሥት ዓመታዊ በጀት ውስጥ 0.5 እስከ 1 በመቶ የሚሆነውን ለዚህ ተግባር እንዲውል የሚፈቅድ ነው። 

ይህ ፈንድ ሰፊ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ምህዳራዊ ጉዳቶችን በማከም ለዓለም አቀፋዊ ትብብር በር ይከፍታል ተብሎ ይጠበቃል።

አረንጓዴ ዐሻራን ተቋማዊ ማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት ለአካባቢ ጥበቃ እና ለአየር ንብረት ጥበቃ ያለውን ከፍተኛ ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ይላል ዥኖዋ። 

የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴርን መረጃ የሚጠቅሰው ሚዲያው አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በአንድ ወቅት ትልቅ ፈተና የነበረውን የአፈር መሸርሸር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ መቻሉን ይጠቁማል።

በዚህም መሰረት ቀድሞ 1.9 ቢሊዮን ቶን አፈር ይታጠብ እንደነበር ነገር ግን አረንጓዴ ዐሻራ መተግበር ከጀመረ ወዲህ ግን ይህ ቁጥር ወደ 208 ሚሊዮን ቶን መውረዱን ጠቅሷል።   

መንግሥት አረንጓዴ ዐሻራን ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ብቻ ሳይሆን ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ዛፎችን በመትከል ለምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ለማድረግ እየሠራ ውጤት እያገኘበት መሆኑንም ዥኑዋ ጠቁሟል። 

በአረንጓዴ ዐሻራ ለምግብነት የሚውሉ ፍራፍሬዎች መተከላቸው የምግብ ዋስትና ላይ የሚያተኩረውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለዘላቂ ልማት ግብ (SDG) 2 ለማሳካት ከፍተኛ ሚና ስላለው ድርጅቱም ዕውቅና መስጠቱ ተጠቅሷል። 

በተጨማሪም አጣዳፊ የአየር ንብረት እርምጃ ከሚያበረታታው የዘላቂ ልማት ግብ (SDG 13) ጨምሮ ከሌሎች ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ግቦች ጋር እንደሚጣጣም ነው በሀተታው የተጠቀሰው። 

መርሐ ግብሩ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት፣ 2030 የዘላቂ ልማት አጀንዳ እና ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ጋር መስማማቱን እና  በዚህ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ተመድ ዕውቅና መስጠቱንም ነው ሚዲያው ያወሳው። 

በቅርቡ በአዲስ አበባ ችግኝ የተከሉት የናይጄሪያው ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሼቲማ የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን መሪነት እንዲከተሉ ጥሪ ማድረጋቸውም ተጠቅሷል። 

መርሐ ግብሩ ለአየር ንብረት ቀውስ ተግባራዊ ምላሽ የሰጠ፣ ለእርሻ ምርታማነት እና ለሥራ ፈጠራ ሰፊ ጥቅም ያለው እንደሆነ መጥቀሳቸውን ነው ዥኑዋ የገለጸው። 

መላውን ኅበረተሰብን ያሳተፈው የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከአፍሪካ ቀንድም አልፎ ለአፍሪካ እና ለዓለም መፍትሔ ይዞ እንደመጣ ነው ዥኑዋ የዘገበው።

በለሚ ታደሰ