ለ1.5 ሚሊዮን ሰዎች የስራ ዕድል የፈጠረውና በ1 ሚሊዮን ሮቦቶች የሚታገዘው አማዞን ኩባንያ

19 Hrs Ago 142
ለ1.5 ሚሊዮን ሰዎች የስራ ዕድል የፈጠረውና በ1 ሚሊዮን ሮቦቶች የሚታገዘው አማዞን ኩባንያ

 

ዛሬ በዓለማችን ካሉት ግዙፍ መደብሮች አንዱ የሆነው የአማዞን ኩባንያ እ.አ. አ. በ1994 በአሜሪካዊው ጄፍ ቤዞስ በአንድ ትንሽ ጋራጅ ውስጥ ነበር  የተመሰረተው።

በወቅቱ ጥቂት መፅሐፍትን በመሸጥ የተጀመረው የአማዞን ጉዞ ዛሬ ላይ በየቀኑ በቢሊዮኖች ግብይት የሚፈጸምበት ኩባንያ እስከመሆን ደርሷል። 

አማዞን በተለያዩ አህጉራት በመቶዎች የሚቆጠሩ መጋዘኖች እና የበርካታ የእቃ መሸጫ መደብሮች ባለቤት ሲሆን፤ ከነዚህ መካከል በሰሜን አሜሪካ ካሉት የአማዞን መደብሮች በግዝፈቱ ሁለተኛ የሆነው የኤም ቲ ጁሊየት የእቃ ማከማቻና መሸጫ የሆነው ትልቅ ሕንጻ ይገኝበታል። 

7 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት የአሜሪካዋ ከተማ ቴኒሲን ነብስ ከዘሩባቸው ትላልቅ ካምፓኒዎች መካከል ከጥቂት ዓመታት በፊት ሥድስት ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው ይህ የኤም ቲ ጁሊየት የአማዞን የእቃ መደብር ዋነኛው ነው።

ከውጭ ሲያዩት ትልቅ መጋዘን የሚመስለው የኤም ቲ ጁሊየት የአማዞን መደብር ረጃጅም የእቃ መደርደሪያ ሼልፎች፣ 3 ሺህ ሰራተኞች እና በሺዎች የሚቆጠሩ አጋዥ ሮቦቶችን የያዘ ነው።

እነዚህ በመጠናቸው አነስተኛ የሆኑ ሮቦቶች እስከ አምስት ኩንታል የሚመዝኑ እቃዎችን የመሸከምና የማመላለስ አቅም ያላቸው ሲሆን፣ በ2012 በአንድ እቃ ማመላለሻ የተጀመረው ሮቦቶችን የመጠቀም ስትራቴጂ ከዓመት ወደ አመት ቁጥሩ እየጨመረ  በቅርቡ  አማዞን በመላው ዓለም በአሉት ከ500 በላይ መደብሮች አንድ ሚሊዮን ሮቦቶችን በስራ ላይ ማዋል ችሏል።

ባለ አምስት ፎቅ ርዝመት ያለው ይህ መጋዘን ሥድስት ሄክታር በሚሆን ቦታ ላይ የተገነባው ባለ አምስት ፎቅ ያለው ሲሆን፤ እያንዳንዱ ወለል የያዘው ቦታ ሲደመር የመጋዘኑ አጠቃላይ ስፋት 3.6 ሚሊዮን ጫማ ስፋት ያለው ግዙፍ መጋዘን ያደርገዋል።

በዚህ የአማዞን መደብር ውስጥ ቢቀጣጠሉ በርካታ ኪሎ ሜትር የባቡር ሀዲድ ሊሰሩ የሚችሉት የእቃ መደርደሪያ ሼልፎች ላይ የአንድ ግራም ያህል ክብደት ካላት ሚሞሪ ካርድ ጀምሮ እስከ ትላልቅ ንብረቶች ድረስ የተሞላ ሲሆን፤ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ የተለያዩ እቃዎችን መያዝ ይችላሉ።

ከ3 ሺህ በላይ ሰራተኞችን ቀጥሮ የ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጠው በኤምቲ ጁሊየት የአማዞን መደብር ውስጥ ያሉ ሰራተኞች ሁሉም በተመደበላቸው ሰዓት ያለ እረፍት ይሰራሉ። ለሸማቾች እቃ ያቀርባሉ ያሳያሉ፣ ያጓጉዛሉ በዚህ መሰረት ቀኑን ሙሉ በመደብሩ ውስጥ እስከ ከ15 እስከ 20 ኪሎ ሜትር ምልልስ ሲያደረጉ ይውላሉ። 

ይህም ማለት እንደ ንብ የሚሰሩት የአማዞን ሰራተኞች በየቀኑ ከግማሽ ማራቶን ርቀት ጋር የሚቀራረብ እንቅስቃሴ እያደረጉ በስራ ቦታቸው ላይ ያሳልፋሉ። 

በዚህ የአማዞን መደብር በየቀኑ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ እቃዎች የሚሸጡ ሲሆን፣ በየ18 ሰከንድ አንድ እቃ ይሸጣል እንደማለት ነው።

የዓለማችን ግዙፉ እቃ አቅራቢ አማዞን በዓለም ዙሪያ በ100 ሀገራት ውስጥ ከሚገኙ አምራቾች ጋር ባለው የንግድ ትስስር በመቶ ሺህዎች ከሚቆጠሩ አምራች ኩባንያዎች ምርቶችን በየጊዜው ያስመጣል። በዚህ ምክንያት የአማዞን መደብሮች ሁሌም ሙሉ ናቸው።

አማዞን ከተለያዩ  ሀገራት እቃ የሚያመላልስባቸው ከ110 በላይ የእቃ መጫኛ አውሮፕላኖች ያሉት ትልቅ ካምፓኒ ነው። በተጨማሪ ግዙፍ መርከቦችን ይከራያል። በነዚህ በራሱ አውሮፕላኖችና በኪራይ መርከቦች አማካኝነት በዓመት 5 ቢሊየን እቃዎች ከመላው ዓለም ወደተለያዩ የአማዞን መደብሮች ይገባሉ።

አማዞን ለአካባቢ ጥበቃ የሚሰጠው ትኩረትም ከፍተኛ ነው። ይህ ካምፓኒ በተለያዩ ሀገራት 20 ሚሊዮን ችግኞችን ተክሏል።

ኩባንያው በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እቃዎች ያሉበትን ትላልቅ መደብሮች በሰው ኃይል ለማስተዳደር እጅግ ከባድ በመሆኑ ዘመን ያፈራቸውን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዙ ኮምፒውተሮችን ይጠቀማል።

የአማዞን መጋዘን ከግዙፍነቱ የተነሳ የቱ እቃ የትኛው ቦታ ላይ እንዳለ ለመፈለግ ያለነዚህ ኮምፒውተሮች እርዳታ ከባድ ነው።

በየወሩ ከ2.5 ቢሊዮን ሰዎች በላይ በሚጎበኘው በዚህ የአማዞን ዌብሳይት ሰዎች የሚፈልጉትን እቃ ያዝዛሉ።

አማዞን በዓለም ዙሪያ ባሉት 620 መደብሮች እና የድረገፅ ግብይቶች ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎችች ቋሚና የትርፍ ጊዜ የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። በመደብሮቹ ውስጥ አጋዥ ሆነው የተለያዩ ስራዎችን የሚሰሩ አንድ ሚሊየን የሚሆኑ የተለያየ መጠንና ስራ ያላቸው ሮቦቶች አሉት።

እያንዳንዱ የአማዞን መደብር በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በሚታገዙ ኮምፒውተሮች በቀልጣፋ ሰራተኞችና ሮቦቶች አማካኝት ግብይቱ እንዲፋጠን ማድረግ የቻለ ሲሆን፣ አንድ ሰው ወደ አማዞን መደብር ገብቶ የሚፈልገውን እቃ ካዘዘ በሁለት ደቂቃ ውስጥ ፍላጎቱን አሟልቶ እቃውን ይጫንለታል።

በአንዲት ትንሽ ጋራጅ  ውስጥ ጥቂት መፅሐፍትን በመሸጥ የተጀመረው የአማዞን ጉዞ ዛሬ ላይ በዓለም ዙሪያ በአንድ ቀን 350 ሚሊዮን እቃዎችን መሸጥ የሚችል ግዙፍ መደብር ለመሆን የበቃ ሲሆን፤ እ.አ.አ. በ2024 ብቻ 638 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘት ችሏል።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top