ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ያስመዘገበችው ስኬት የአፍሪካ ዕድገት እውን እንደሚሆን ሁነኛ ማሳያ ነው ሲሉ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ገለጹ።
ኦባሳንጆ ሐሙስ ዕለት በናይጄሪያ መዲና አቡጃ መካሄድ በጀመረው 32ኛው የአፍሪኤግዚም ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ አፍሪካውያን መሪዎች የአህጉሪቱን ዕድገት እውን ለማድረግ የየሀገራቸውን የአስተዳደር ሥርዓት ዳግም ማጤን አለባቸው ብለዋል።

የአህጉሪቱ ዕድገት የመሪዎቿ በጋራ መሥራት እና ወደፊት መራመድ አቅም እንዲሁም የአህጉሪቱን ጥቅም ማስቀደም ብቃት ላይ የተመሠረተ እንደሆነም ነው የጠቆሙት።
ከቅኝ ግዛት ኃይሎች የወረስነው የምዕራቡ ሊበራል ዴሞክራሲ ሥርዓት የአፍሪካን ጥቅም በማስከበር ረገድ ውጤት ያስገኘ ባለመሆኑ ሊገመገም እና ለአህጉሪቱ በሚመጥን መልኩ ሊሆን ይገባል ሲሉ አስገንዝነበዋል።
“አንበሶቹ” በሚል ስም የገለጿቸው የአፍሪካ ኃያላን እና ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑት ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ ግብጽ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ሴናጋል እና ሞሮኮ አሁን ከደረሱበት ደረጃ የበለጠ መሔድ የሚችሉ ነበሩ ብለዋል የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ።
እነዚህ ሀገራት መድረስ የነበረባቸው ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ምን ማድረግ አለባቸው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የሀገራቱ መሪዎች የዓለምን ውብስብስ ኢኮኖሚ የሚረዱበት እውቀት ማካባት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
አፍሪካ በውጭ ሀገራት ዕርዳታ ላይ ጥገኛ መሆኗ የአህጉሪቱን ዕድገት ገድቦታል ያሉት ኦባሳንጆ፤ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን ከመቻል አልፋ ወደ ገረቤት ሀገራት መላክ መጀመሯን ጠቅሰው፣ ይህም የአፍሪካ ዕድገት እውን መሆን እንደሚችል ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።
ይህ የኢትዮጵያ እመርታ የመጣው ታዲያ በበሳል አመራር ሰጪነት በመሆኑ ሌሎች የአፍሪካ መሪዎችም ይህንኑ ተግባራዊ እንዲያደርጉ መክረዋል።
የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት በስንዴ ምርት ላይ የፈጠረው ቀውስ በተለይ ለአፍሪካ ከባድ እንደነበር አስታውሰዋል።
የኮቪድ ወረርሽኝን ጨምሮ ወቅቱ ከባድ ቢሆንም በዚህ ጊዜ ግን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በስንዴ ምርት ራስን የመቻል እቅድ ይፋ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ስሟ ከአስከፊ ድርቅ ጋር ይነሣ ነበር ያሉት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ዕቅድ ታሪክ ቀያሪም ጭምር መሆኑን ነው የተናገሩት።
“በአምስት ዓመት ከስንዴ ተረጅነት ወጥተን ለውጭ ገበያ እናቀርባለን” የሚል ዕቅድ ይዘው ሥራ ጀምረው የነበረ ቢሆንም ይህን ዕቅድ በሦስት ዓመታት ውስጥ ማሳካት ችለዋል ሲሉ ነው ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ስለኢትዮጵያ የስንዴ ልማት የገለጹት።
አሁን ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለጎረቤት ሀገራትም ጭምር ስንዴ እያቀረበች መሆኗን ገልጸው፣ ይህ ስኬት ለአፍሪካ ጥሩ የሕዳሴ ማብሰሪያ ምልክት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ይህን ማሳካት ከቻለች አፍሪካውያን ብዙ መሥራት እንችላለን ማለት ነው ያሉት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አፍሪካ ሕዳሴዋን ማብሰር እንደምትችል ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

መሪዎቻችን 20 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ወደ ቻይና ይሮጣሉ፤ ያ 20 ቢሊዮን ዶላር ግን ከአንድ የአፍሪካ ሀገር ሊገኝ የሚችል ነው፤ የእርስ በርስ ትሥሥሩን ትተን ወደ ሌሎች መሮጣችንን ከቀጠልን ነገሮች ትክክል አይሆኑም ሲሉ ገልጸዋል።
በሀገር ውስጥ ገንዘቦች ከአንዱ የአፍሪካ ሀገር ወደ ሌላኛው ሀገር ገንዘብ ለመላክ የሚያስችለው የአፍሪኤግዚም የክፍያ ሥርዓት “PAPSS” ሊበረታታ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
ይህም የአፍሪካ መሪዎችን በጋራ ለመሥራት እና ወደ ፊት ለመራመድ እንዲሁም የአህጉሪቱን ጥቅም ለማስጠበቅ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
በሌላ በኩል የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) የኢኮኖሚ ውህደት እና የትብብር ማዕቀፍ በማበርከት የአፍሪካ የእርስ በርስ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ አበርክቶ እያደረገ ነው ብለዋል።
በእነዚህ እመርታ ባስመዘገብንባቸው ጉዳዮች ላይ የበለጠ መሥራት እና ወደ ፊት መራመድ አለብን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
እርስ በርሳችን መማማር አለብን፤ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ አንበሶች መድረስ ካለባቸው ላይ ሲደርሱ ደቦሎቹም ይከተላሉ ብለዋል ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ።