በጉርምስና የእድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ልጆች ጋር ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ምን መምሰል አለበት? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ የቅዳሜ መልክ የዜና መሰናዶ የልጆች ሁለንተናዊ እድገት ባለሙያ ከሆኑት ዶ/ር ቱሚም ጌታቸው ጋር ቆይታ አድርጓል።
በተፈጥሮ ልጆች የሚኖራቸውን የአካላዊ እንዲሁም የሆርሞን ለውጥን ተከትሎ፤ እንዲሁም የጓደኛ እና ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ በማሕበራዊ ሚዲያ በሚመለከቷቸው ነገሮች የሚፈጠሩባቸው ተፅእኖዎች በአጠቃላይ ከወላጆቻቸው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ላይ ተፅእኖ እንዳለው ዶ/ር ቱሚም ይገልጻሉ።
የወላጅ የእውቀት እንዲሁም የልምድ ደረጃ እና የልጆች የእውቀት ደረጃ እጅግ ልዩነቱ እየሰፋ በሚመጣበት ወቅት፤ አንዱ አንዱን ለመረዳት የሚኖረው ክፍተት ሰፊ ሊሆን እንደሚችልም ያነሳሉ።
በዚህ ወቅት በተለይ በጉርምስና የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆችን ወላጆች ማዳመጥ፣ መደገፍ እንዲሁም ጊዜያቸውን መስጠት ካልቻሉ፤ ልጆች ማንም አይረዳኝም ወደሚል አስተሳሰብ ሊገቡ እንደሚችሉም ነው የጠቆሙት።
ይህን ተከትሎም ይረዳናል ብለው ወደሚያስቡት ሰው፣ ጓደኛ ወይም ሶሻል ሚዲያ ላይ ወደ ተዋወቁት ወደማያውቁት ሰው ሊሔዱ፤ መፍትሄ ሊፈልጉ እንደሚችሉ ዶ/ር ቱሚም ይገልጻሉ። ይህም ልጆችን ወደ ሌላ ችግር ሊገፋቸው እንደሚችልም ነው የሚያነሱት።
ወላጆች በየጊዜው ከልጆቻቸው ጋር መነጋገር እንዲሁም ሀሳባቸውን መካፈል እንደሚኖርባቸው ጠቁመው፤ በሕይወታቸው ውስጥ የተፈጠረውን ነገር እንደ ጓደኛ በመረዳት የመፍትሔ ሀሳቦች ላይም በጋራ በመነጋገር መፍትሔ መፈለግ እንዳለባቸው ባለሙያዋ ይናገራሉ።
በዚህ ሁኔታ የሚመሰረት ግንኙነት ቀስ በቀስ እርስ በእርስ ወደ መግባባት የሚያድግ በመሆኑ፤ ወላጆች ለልጆቻቸው በቀን ውስጥ የሚያወሩበት ወይም የሚጫወቱበት የተወሰነ ሰዓት ሊመድቡ እንደሚገባ ይገልጻሉ።
የቤተሰብ ጊዜ ሲኖር አብሮ የመጫወት ጊዜ ስለሚኖራቸው የልጆቻቸውን ባህርይ ለመረዳት፤ እንዲሁም ከልጆቻቸው ጋር ጥሩ ግንኙነት የሚፈጠርበት ሁኔታ ሰፊ የመሆን እድል እንደሚኖረው ባለሙያዋ አንስተዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ