ሩብ ምዕተ አመቱን ለያዘው የአለም ክለቦች ውድድር ፊፋ ያዘጋጀው ዋንጫ በቅርጽም በአይነትም የተለየ ሆኖ ታሪክንም አሁንንም እንዲገልጥ ሆኖ የተዘጋጀ ነው።
በአሜሪካ አዘጋጅነት ሲካሄድ ቆይቶ ትናንት በቼልሲ አሸናፊነት በተጠናቀቀው የፊፋ የአለም ክለቦች ውድድር ላይ ለአሸናፊው ክለብ የተበረከተው ዋንጫ በአይነቱ የተለየ ነው።
ይህ ዋንጫ የታላላቅ ስፖርታዊ ውድድሮች ሽልማቶችን በመስራት ታዋቂ የሆነው ቲፋኒ ኩባንያ የተሰራ ሲሆን ከንፁህ ብር ተሰርቶ በ24 ካራት ወርቅ የተለበጠ ነው።
እአአ በ1977 ወደ ጠፈር የተላኩትን ቮይጀር አንድ እና ሁለት ሰው አልባ መንኮራኩሮችን መሰረት በማድረግ የተነደፈው ይህ በአይነቱ የተለየ ዋንጫ ከዳር እስከዳር 44 ሳንቲ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን አምስት ኪሎ ግራም ክብደት አለው።
በዋንጫው ላይ የ211ዱም የእግር ኳስ አባል ሀገራት፣ የ6ቱ ኮንፌደሬሽኖች ስም እና ፊፋ የተመሰረተበትን ቀንየያዘ ሆኖ የተቀረጸ ነው።
እግር ኳስ ያለፈባቸውን መንገዶች እና አሁን ያለበትን ደረጃ እንዲያሳይ ሆኖ የተቀረጸው ዋንጫ የፊፋ የመጀመሪያው ህግ እና የክለቦች አለም ዋንጫ የተጀመረበት ቀን እንዲሁምበተመሳሳይ የዚህ አመቱ ውድድሩ የተጀመረበት ዕለት ተፅፎበታል።
በተለይ የዋንጫው መሀለኛው ክፍል በርካታጉዳዮች ያሉበት ሲሆን በዋናነት የአለም ካርታን እና የእግር ኳስ ታሪክ እንዲሁም ባህልን በሚገባ የሚያሳይ ሆኖ ተቀምጧል።
እግር ኳስ አካታች መሆኑን በሚገባ እንዲያሳይ ሆኖ የተዘጋጀው አዲሱ የክለቦች አለም ዋንጫ ቅርፁን መቀያየር እንዲችልተደርጎ የተሰራ ሲሆን ከዋንጫው ጋር አንድ ላይ የሚሰጥ መክፈቻ ቁልፍም ተሰርቶለታል።
ይህ ከንፁህ ወርቅ የተሰራ ቁልፍ የሚያገለግለውየዋንጫውን ቅርፅ ለመለወጥ ሲሆን ከዋንጫው ጀርባ በተዘጋጀው የቁልፍ ማስገቢያ ውስጥ በማድረግ ሲያዞሩት ጠፍጣፋና ክብ መሳይ ቅርፅ ከነበረው የዋንጫው መዋቅር ውስጥ የነበሩ ትላልቅ ቀለበታማ ክፍሎች መንቀሳቀስ ይጀምሩና በመሀል ያለውን ዲስክ እንደምህዋር ተጠቅመው መዞር ይጀምራሉ በዚህ መሰረት ወርቃማው ዋንጫ ጋሻ መሰል ቅርፁን ትቶ የፕላኔቶችንና የምህዋር አይነት መልክ ይይዛል።
በ13 የተለያዩ ቋንቋዎች የተለያዩ መልዕክቶችንያዘው እና እስከአሁን ከተሰሩት የተለየው ዋንጫ ከዲዛይን ጀምሮ ለመስራት ከ500 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በላይ እንደወሰደ የሚገመት ሲሆን በቅርስነቱና በታሪካዊነቱ እስከ ሀያ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ዋጋ ያለው ነው።