ከአነስተኛ የሩዝ መሸጫ መደብር የተነሳው ግዙፉ ሳምሰንግ ኩባንያ

4 Hrs Ago 503
ከአነስተኛ የሩዝ መሸጫ መደብር የተነሳው ግዙፉ ሳምሰንግ ኩባንያ

ከአነስተኛ የሩዝ መሸጫ መደብር የዓለማችንን ግዙፍ ሕንጻዎች እስከመገንባት የደረሰው የሳምሰንግ የፈተናና የስኬት ጉዞ ብዙ የተባለለት ነው።

የዚህ የዓለማችን ግዙፍ ሁለገብ ኢንደስትሪ ታሪክ የሚጀምረው ከትንሽ ግሮሰሪና ሱ ዶንግ ከምትባል አነስተኛ ከተማ ነው።

እ.አ.አ. በ1938 በደቡብ ኮሪያ በምትገኘው ትንሽየዋ ሱ ዶንግ ኮሪያዊው ሊ ቢዩን-ቹል ሳምሰንግ ሲል በሰየማት ትንሽ ግሮሰሪ የደረቀ አሳ፣ አትክልቶችን፣ ሩዝ እና ለአስቤዛ የሚሆኑ እቃዎችን መሸጥ ጀመረ።

በወቅቱ ይህ በግሮሰሪ የተጀመረ ንግድ አድጎ እንደወረቀት የሚታጠፉ ቴሌቪዥኖችንና ስልኮችን፣ ከፍ ሲልም ውቅያኖስን የሚሻገሩ ግዙፍ መርከቦችን እየሰራ ለሀገሩ ኤኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሚሆን ግዙፍ ኩባንያ ይሆናል ብሎ ማንም አላሰበም ።

ሆኖም በዚህ መልኩ የተጀመረው የስኬት ግስጋሴ ከቀን ወደቀን እየሰፋ በ1970 ዎቹ ሳምሰንግ የኤሌክትሮኒክስ ምርቱን ዓለም ተቀላቀለ።

በዚህ ጅምሩም በጃፓኑ ሳንዮ ኩባንያ እገዛ የመጀመሪያው የሆነውን ቴሌቪዥን አምርቶ ለገበያ አቀረበ።

በዛን ወቅት በሳንዮ የቴክኖሎጂ እገዛ የቴሌቪዥን ገበያውን የተቀላቀለውም ሳጥን የሚመስል ጥቁርና ነጭ ቴሌቪዥን በመስራት ነው።

በዚህ መልኩ የተጀመረው የሳምሰንግ ቴሌቪዥን ቴክኖሎጂ አድጎ ዛሬ ላይ የዓለማችንን የቴሌቪዥን ገበያ 28 በመቶ መቆጣጠር ችሏል። ላለፉት ተከታታይ 17 ዓመታትም በዓለም ግንባር ቀደም የቴሌቪዥን አምራች ኩባንያ ሆኖ ቀጥሏል።

ገና ከጅምሩ ትልቅ ህልምና ራእይ ይዞ የተነሳው የሳምሰንግ ጉዞ እዚህ ላይ አልቆመም በደረሰበት የስኬት ደረጃ ከመርካት ይልቅ ይበልጥ ገናና ለመሆን እርምጃውን ቀጠለ።

በተለይ በኤሌክትሮኒክስ ዘርፉ ስኬት በማስመዝገብ ፍሪጆች የልብስ ማጠቢያና የተለያዩ እቃዎችን ማምረት ጀመረ። በተለይ የስማርት ስልኮች መምጣት ለዚህ ካምፓኒ መመንደግ ምክንያት ሆነለት ።

ሳምሰንግ ይህንን ሁኔታ እንደምቹ አጋጣሚ ተጠቅሞም እ.አ.አ. በ2010 ላይ ሳምሰንግ ጋላክሲ ኤስ የተሰኘችውን አነስተኛ መጠን ያላት ስልክ አምርቶ ለገበያ አቀረበ።

ዛሬ ላይ ሳምሰንግ ከኤሌክትሮኒክስ ቀለበት እቃና ነዳጅ እስከሚጭኑ ግዙፍ መርከቦች ድረስ ያመርታል።

ሳምሰንግ በስሩ ከ1 ሺህ በላይ ፋብሪካዎች አሉት። በዓለም ዙሪያ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰራተኞችን የሚያስተዳድር ሲሆን፤ የራሱ የሆነ ግዙፍ ስማርት ሲቲ መገንባት የቻለ ኩባንያም ሆኗል።

ሳምሰንግ ከኤሌትሮኒክስ ምርቶቹ በተጨማሪ ግዙፍ መርከቦችን የሚያመርት ትልቅ ተቋምም አለው። ጉዎጂ በምትባለው የኮሪያ የባህር ዳርቻ በሚገኘው የሳምሰንግ ኢንደስትሪ ማእከል የመርከብ ኢንጂነሮች ከእግር ኳስ ሜዳ ሶስት ጊዜ የሚበልጥ ርዝመት ያላቸውን መርከቦች ዲዛይን ሲሰሩ ውለው ያድራሉ።

ትላልቅና ወፍራም ላሜራዎች ተጣጥፈው ተቆራርጠውና ተበይደው ወደ ግዙፍ መርከብነት በሚቀየሩበት በዚህ የሳምሰንግ ማእከል በየዓመቱ አስር የሚደርሱ ዋጋቸው በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች የሆኑ ትላልቅ የነዳጅ እና የእቃ ጫኝ መርከቦች ይሰራሉ።

ሳምሰንግ በዚህ የግዙፍ መርከቦች መስሪያ ኢንደስትሪው ውስጥ ከሰራቸው ግዙፍ መርከቦች ውስጥ “MSC Gülsün” የሚል ስያሜ ያላት ኮንቴነር ጫኝ መርከብ ትገኝበታለች።

ይህች በሳምሰንግ ኢንጂነሮች ተነድፋ የተገነባችው ግዙፍ መርከብ 400 ሜትር ርዝመት እና 61 ሜትር ስፋት ያላት ሲሆን፤ በእቃ የተሞሉ 23,756 ኮንቴነሮችን የመጫን አቅም ያላት በዓለማችን ከሚገኙ ግዙፍ ኮንቴነር ጫኝ መርከቦች መሀከል አንዷ ናት።

ዘርፈ ብዙው ሳምሰንግ በኮንስትራክሽኑ ቢዝነስ ውስጥም በዓለማችን ትላልቅ የሚባሉ ሰማይጠቀስ ህንጻዎችን መገንባት የቻለ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ እ.አ.አ. በ2010 የተገነባውና 828 ሜትር የሚረዝመው የዓለማችን ትልቁ ህንጻ የዱባዩ ቡርጅ ከሊፋ አንዱ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ በኳላላምፑር የገነባው ባለ 679 ሜትር ረጅም ህንጻ፣ በታይዋን የሰራው 508 ሜትር ቁመት ያለው ሰማይጠቀስ ፎቅ፣በህንድ፣ በሲንጋፖር እንዲሁም በደቡብ ኮሪያ ትላልቅ ህንጻዎችን ከሳምሰንግ የኮንስትራክሽን ግንባታ ውጤቶች መካከል ናቸው።

ሳምሰንግ ዛሬ የሩዝ ፍሬ ከሚያካክሉ ማይክሮ ቺፕስ እስከ ግዙፍ መርከቦች የሚሰሩበት፤ ለኮሪያ የጀርባ አጥንት የሆነ ኢንደስትሪ ሆኗል።

ይህ ሲባል ሳምሰንግ ምንም አይነት ፈተና ገጥሞት አያውቅም ማለት አይደለም። ሳምሰንግ በዚህ የረጅም ዓመት ጉዞው ከገጠሙት ፈተናዎች አንዱ እ.አ.አ. በ2016 ላይ የተከሰተው ያልታሰበ የቴክኖሎጂ ስህተት ይገኝበታል።

ይህ ወቅት ሳምሰንግ ኖት 7 የተባለውን አዲስ ስልክ ሰርቶ ለገበያ ያቀረበበት ጊዜ ነበር። ይህ ስልክ ለገበያ የቀረበው ከጊዜ ወደ ጊዜ ምርቱን እያሻሻለ የመጣበት እና የሳምሰንግ ስልኮች ተወዳጅ እየሆኑ የመጡበት ወቅት ነበርና ሳምሰንግ ይህንን ኖት 7 የተባለ ስልክ ለገበያ ላይ እንዳዋለ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ3 ሚሊዮን ስልኮች በላይ ተሸጡ።

ሆኖም እነዚህ ስልኮች ገበያ ላይ እንደዋሉ በተጠቃሚውና በካምፓኒው ዘንድ ድንጋጤን የሚፈጥር ነገር ተከሰተ። ይኸውም እነዚህ አዲስ የቀረቡት የሳምሰንግ ስልኮች በባትሪያቸው ላይ በተፈጠረ ስህተት ሙቀት የሚፈጥሩና የሚፈነዱ ነበሩ።

በወቅቱ የአሜሪካ ሳውዝ ዌስት አየር መንገድን አውሮፕላን ለመሳፈር ይጠባበቅ የነበረ አንድ መንገደኛ ከስልኩ ጋር በተያያዘ አደጋ ካጋጠመው በኋላ የሳምሰንግ አዲስ ስልክ ጉዳይ ትልቅ ችግር መፍጠር ጀመረ።

በዚህ እለት ከሉዊቪል ኬንተኪ ወደ ባልቲሞር ለመጓዝ በመጠባበቅ ላይ የነበረው ይህ መንገደኛ በኪሱ ውስጥ የነበረው አዲስ የሳምሰንግ ኖት 7 ስልክ መሞቅ ጀመረ ፤ ተሳፋሪው በኪሱ ውስጥ የነበረውን ስልክ አውጥቶ ሲጥለው ስልኩ ጭስ ማውጣት ጀምሮ ነበር።

ሆኖም ዜናው ድንጋጤን ፈጠረ። በተለይ ይህ አደጋ የተከሰተው በአውሮፕላኑ ውስጥ ከገባ በኋላ ቢሆን ኖሮ የከፋ አደጋ ይከሰት እንደነበር በማሰብ በመላው ዓለም የሚገኙ አየር መንገዶች ኖት 7 ስልክን ተሳፋሪዎች ይዘው እንዳይጓዙ በይፋ አገዱ።

ይህ ከተከሰተ ከቀናት በኋላ በኖት 7 ምክንያት የተፈጠሩ ጉዳቶች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ይሰሙ ጀመር። በአውስትራሊያ በአንድ የሆቴል ክፍል ቻርጅ ላይ የነበረ ኖት 7 በፈጠረው ፍንዳታ መጠነኛ የእሳት አደጋ ተከሰቶም ነበር።

በአሜሪካ ስልኩን ከገዙ ከ90 ሰዎች በላይ ስልኩ እንደጋለ እና እንደተቃጠለ አመለከቱ። በደቡብ ኮሪያ አውስትራሊያ እንግሊዝ ቻይና እና ካናዳም ተመሳሳይ ችግሮች ተመዘገቡ። በአንዳንድ ሀገራት በስልኩ ባትሪ ፍንዳታ የተነሳ በሰዎች ላይ፣ በመኪና ፣ በመኖሪያ ቤቶች እና በሆቴል ክፍሎች ላይ ጉዳይ አስከትሏል የሚሉ ክሶች በሳምሰንግ ላይ ተመሰረቱ ።

ይህ ያልታሰበ ስህተት በሳምሰንግ ኩባንያ ላይ ድንጋጤ መፍጠሩ አልቀረም። ሆኖም ኩባንያው ወደ መፍትሄ ሄደና የተሸጡትን ስልኮች ሁሉ ከመላው ዓለም መሰብሰብ ጀመረ። በዚህም 2.7 ሚሊዮን ስልኮች ተሰብስበው ለገዥዎቹ ገንዘባቸው እንዲመለስ ተደረገ።

በዚህ አስደንጋጭ ክስተት ምክንያት ሳምሰንግ ኖት 7 ስልኮችን ዳግም እንዳይመረቱ ወሰነ። በዚህም ሳምሰንግ በቀጥታ ከ5 እስከ 6 ቢሊየን ዶላር ኪሳራ ስላጋጠመው ከገበያ ድርሻው 17 ቢሊዮን ዶላር አጥቷል።


ከዚህ በኋላ ሳምሰንግ የባትሪዎችን ጥራት የሚቆጣጠርና የሚመረምር ራሱን የቻለ ቡድን አቋቋመ። የሳምሰንግ ስልክ ባትሪዎች ከመገጠማቸው በፊት ስምንት የጥራት ሂደቶችን ማለፍ እንዳለባቸው የሚያስገድድ ሕግ አወጣ።

ከአንድ ዓመት በኋላም ሳምሰንግ ጋላክሲ ኖት ፈን በሚል እጅግ ጥራት ያለው ስልክ በማምረት ወሰገበያው ተመለሰ። ዛሬ ላይ እጅግ ተመራጭ ዘመናዊ ስልኮችን በማምረት የዓለማችንን አንድ አምስተኛ ዕጅ የስልክ ፍላጎት የሚያሟላ ካምፓኒ ሆኗል። በሳምሰንግ ቴክኖሎጂ ማእከል ከስልክ በተጨማሪም ከሰው ጋር በንግግር መግባባት የሚችሉ ፍሪጆች ሁሉ ይመረታሉ።

በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ታግዞ የሚሰራ ዘመናዊ ፍሪጅ በውስጡ በተገጠሙለት ካሜራዎች አማካኝነት በማቀዝቀዣው ውስጥ ያሉትን እቃዎች አይነት መለየት ይችላል። ከስልክ ጋር ባላቸው የኢንተርኔት ግንኙነት ከርቀት ሆኖ በፍሪጁ ውስጥ ምን እንዳለ ማየት ይቻላል።

ይህ ብቻ አይደለም እነዚህ የሳምሰንግ ፍሪጆች በውስጣቸው ያለውን አትክልት፣ እንቁላል ስጋ እና የመሳሰሉትን ነገሮች በመጠቀም ምን ሰርተው መመገብ እንደሚችሉ ከመንገርም ባለፈ ላያቸው ላይ በተገጠመው ስክሪን ሊሰሩት የሚችሉትን የምግብ አይነት አሰራር ማሳየት ይችላሉ። የአገልግሎት ጊዜያቸውን በማረጋገጥ የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት ምግብ ወይ መጠጥ ካለ ይናገራሉ።

በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚታገዙትን እነዚህን ፍሪጆች ምን ምግብ እንዳለቀ፣ ምን መታዘዝ እንዳለበት በንግግር መጠየቅ የሚቻል ሲሆን፤ መገዛት ያለበት አስቤዛ ካለ እንዲገዛ በስልክ ወይም በላያቸው ላይ ባለው ስክሪን ያሳውቃሉ።

ከትንሽ የአትክልት መሸጫ ግሮሰሪ ተነስቶ በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች በማለፍ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ የደረሰው ሳምሰንግ ለብዙ ስራ ፈጣሪዎች የፅናትና የስኬት ተምሳሌት ሆኖ ጉዞውን ቀጥሏል።

በዋሲሁን ተስፋዬ 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top