ኬንያ ለኮሮና ከተለያዩ ለጋሾች የተሰጠው እርዳታ መዘረፉን አስታወቀች

3 Yrs Ago
ኬንያ ለኮሮና ከተለያዩ ለጋሾች የተሰጠው እርዳታ መዘረፉን አስታወቀች

የኬንያ የወንጀል ምርመራ ፖሊሶች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከቻይናው ቢሊየነርና የአሊባባ ኩባንያ ባለቤት ጃክ ማ ተልከው የነበሩ ቁሳቁሶች እና ከተለያዩ ለጋሾች የተሰጡ እርዳታዎች የት እንደገቡ አልታወቀም።

የኬንያ ፖሊስ እንደሚለው የኬንያ መንግሥት የተሰረቀው ለኮሮናቫይረስ የተላኩ በርካታ ቁሳቁሶች ብቻ ሳይሆኑ በሚሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብም ጭምር ነው፡፡

የጤና መጠበቂያ ቁሳቁሶቹ የቀዶ ጥገና ጓንቶች፣ የአፍ አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች፣ የሙቀት መለኪያ መሣሪያዎችና በሐኪሞችና ነርሶች የሚለበሱ ጋውኖችን ያካተተ ነው፡፡

የኬንያ ፖሊስ ይህን መግለጫ የሰጠው ኬቲኤን የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ከቻይና መንግሥት በእርዳታ የተሰጠ ግምቱ 2 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የሕክምና ቁሳቁስ እንዴት እንደተሰወረ ካጋለጠ በኋላ ነው፡፡

ቴሌቪዥን ጣቢያው ባሰራጨው የምርመራ ዘገባ አንድ ከመንግሥት ባለሥልጣናትና ከቻይና ባለሀብቶች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የሚሰራ የግል ኩባንያ እነዚህ እርዳታዎች ኬንያ አየር መንገድ ሲደርሱ ይህ ኩባንያ የቁሳቁሶቹ ተረካቢ ሆኖ እንደቀረበ ያጋልጣል፡፡

ኬንያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ከቻይናው ቢሊየነር ጃክ ማ በተጨማሪ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይኤምኤፍ እና ከአውሮጳ አገራት እርዳታ ተለግሷታል፡፡

ሆኖም የኅብረተሰብ ጤና ባለሞያዎች የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት ገጥሟቸዋል፡፡ ይህ እጥረት በልገሳ የተገኙ ቁሳቁሶች የት ገቡ የሚል ጥያቄ አስነስቶ ቆይቷል፡፡

የኬንያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሙታይ ካግዌ ሌቦቹን የገቡበትን ገብተን እንይዛቸዋለን ሲሉ ዝተዋል፡፡

ኬንያዊያን ፌስቡክን በመሰሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ያለውን ሙስናና መንግሥታቸው ሙሰኞችን ለመያዝ የሚያሳየው ዳተኝነት እንዳስቆጣቸው እየገለጹ ነው፡፡

በኬኒያ እስካሁን 3 ሺህ 860 ሰዎች በኮሮና መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 105 ሰዎችም በወረርሽኙ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከበሽታው 1 ሺህ 328 የሚሆኑት ደግሞ አገግመዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top