የሕጻናት እና ሴቶች ሰቆቃ የሆነው የእስራኤል እና ሃማስ ገጭት መቋጫው ምን ይሆን?

8 Mons Ago
የሕጻናት እና ሴቶች ሰቆቃ የሆነው የእስራኤል እና ሃማስ ገጭት መቋጫው ምን ይሆን?

ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የደረሱ ጥፋቶች

አጀልዚራ ባለፈው ዐርብ ባወጣው መረጃ መሰረት በእስከ አሁኑ የሁለቱ ወገኖች ግጭት በጋዛ እና እስራኤል በያዘችው ዌስት ባንክ ቢያንስ 15 ሺህ 83 ሰዎች መሞታቸውን፣ ከነዚህ ውስጥም 6 ሺህ 202 ህጻናት፣ 4 ሺህ ሴቶች መሆናቸውን ገልጿል። 35 ሺህ 750 ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ 6 ሺህ 800 ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም።

ወደ 1.7 ሚሊዮን የሚጠጉ ፍልስጤማውያን ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በእስራኤል ሠራዊት በመገደድ ወደ ደቡባዊው የየጋዛ ሰርጥ አካባቢዎች ሸሽተዋል።

ይህን ቁጥር ወደ ሰዓት የቀየረው አልጀዚራ በጋዛ በየአንድ ሰዓቱ 15 ሰዎች ሲሞቱ ከነዚህ ስድስቱ ህጻናት መሆናቸውን አመልክቷል። 35 ሰዎች ደግሞ በያንዳንዱ ሰዓት ይቆስላሉ፡፡ በተጨማሪም በያንዳንዱ ሰዓት 42 ቦምቦች የሚጣሉ ሲሆን፣ 12 ህንጻዎችን ይወድማሉ።

በእስራኤል ወገንም 1 ሺህ 200 ሰዎች ሲሞቱ፣ 5 ሺህ 600 ሰዎች ቆስለዋል፡፡ እስራኤል የሟቾቹን ቁጥር 1 ሺህ 500 እንደሆነ ትገልጻለች።

በሌላ የአልጀዚራ መረጃ መሰረት ደግሞ በዚህ ግጭት ቢያንስ 53 ጋዜጠኞች የተገደሉ ሲሆን፣ ከነዚህ ጋዜጠኞች 46 ፍልስጤማውያን፣ አራት እስራኤላውያን እንዲሁም ሦስት ሊባኖሳውያን ይገኙባቸዋል።

2.3 ሚሊዮን ሕዝብ ተጠጋግተው የሚኖሩባት ጋዛ መውጫ መግቢያው በእስራኤል እጅ ነው፡፡ እ.አ.አ ከ2007 ጀምሮ ላለፉት አሥራ ሰባት ዓመታት እስራኤል የጋዛን የአየር ክልል እና የየብስ እንቅስቃሴ በመያዝ የሰዎችን እና የሸቀጦችን ወደ ጋዛ መግባት እና መውጣት ትቆጣጠራለች።

በአሁኑ ግጭት በዓለም አቀፍ ሕግ ከጦርነት ቀጠና ነጻ መሆን የሚገባቸው እንደ የሃይማኖት ተቋማት፣ሆስፒታሎች እና ትምህርት ቤቶች ከሃማስ መሸሸጊያነት ከእስራኤል ጥቃት ሊያመልጡ አልቻሉም።

እ.አ.አ ጥቅምት 7 ሃማስ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ከተኮሰበት ዕለት ጀምሮ እስራኤል በተከታታይ በወሰደቻቸው የአየር ድብደባዎች 278 ሺህ መኖሪያ ቤቶች፣ 311 የትምህርት ተቋማት፣ 87 አምቡላንሶች እና 11 ዳቦ ቤቶች ወድመዋል።

 

ከዚህ ቀደም በሁለቱ ወገኖች የተደረጉ የተኩስ አቁም ስምምነቶች እና ፈተናዎቹ

አል ሻባካ የተባለው የፍልስጤም የምርምር ተቋም ውስጥ የሚሰራው ታሬቅ ባኮኒ እንደገለፀው ሃማስ እና እስራኤል እ.አ.አ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ "በአስከፊ ፍጥጫ" ውስጥ ይገኛሉ። የ2006ቱን የፍልስጤም ምርጫ ያሸነፈው ሃማስ በ2007 የጋዛ ሰርጥን በቁጥጥሩ ሥር አዋለ፤ እስራኤልም አካባቢውን በመዝጋት ከሃማስ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገባች። ይህም በጋዛ ከፍተኛ ድህነት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል፤ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች የምግብ እርዳታ ጠባቂ ሲሆኑ፣ የጤና እንክብካቤ ማግኘት ደግሞ ቅንጦት ሆኗል። በጋዛ የሚኖሩ አንድ አራተኛ የሚሆኑት ፍልስጤማውያን እና 80 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች ሥራ አጥ ሆነዋል።

በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተካሄዱ ጦርነቶችን ለማስቆም የተደረጉ የሰላም ውይይቶችን የተመለከቱ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት እያንዳንዱ ግጭት በሦስተኛ ወገኖች አደራዳሪነት ለጊዜው ጋብ ካለ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ተመልሰው ግጭት ውስጥ ይገባሉ። የሰላም ውይይቶች በየጊዜው የተካሄዱ ቢሆንም ግጭቶቹን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም የማያዳግም እልባት ሊያስገኝ ከሚችል ትልቅ ፖለቲካዊ ውሳኔ ላይ ሊደረስ አልተቻለም።

እ.አ.አ 2008-2009 ለ22 ቀናት በቆየ የእስራኤል ኦፕሬሽን 1 ሺህ 400 ፍልስጤማውያን፣ እንዲሁም 10 የእስራኤል ወታደሮች እና ሶስት ሲቪሎች ተገድለው ነበር። የወቅቱ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮንዶሊዛ ራይስ ሁለቱን ወገኖች አደራድረው የተኩስ አቁም ስምምነት አፈራረሙ።

የተኩስ አቁሙ የጎላ ግጭት ሳይፈጠር እ.አ.አ እስከ ኅዳር 2012 ዓ.ም ድረስ የቆየ ሲሆን፣ በዚሁ ዓመት ለስምንት ቀናት የቆየ ግጭት ተከስቶ 167 ፍልስጤማውያን እና ስድስት እስራኤላውያን ሞቱ። በወቅቱ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄላሪ ክሊንተን አማካኝነት ሌላ የሰላም ስምምነት ፈጸሙ።

ስምምነቱ እ.አ.አ በ2014 ከቆየ በኋላ በዚሁ ዓመት እንደገና ለ50 ቀናት የቆየ ጦርነት ተከስቶ 2 ሺህ 251 ፍልስጤማውያን እና 67 የእስራኤል ወታደሮችን ቀጠፈ። ይህ ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ሁለቱን ወገኖች ያደራደረ ወገን የለም።

ጦርነቱ እ.አ.አ በግንቦት 2021 እንደ ገና ተቀስቅሶ ለ11 ቀናት የዘለቀ ሲሆን፣ 230 ፍልስጤማውያን እና 12 እስራኤላውያን ሞተዋል። ሃማስን በአሸባሪነት የፈረጀችው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ግጭቱ እንዲቆም ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ጋር ውይይት አድርገው ከስምምነት ላይ ሲደርሱ ግጭቱ ለጊዜው ጋብ አለ።

የአሁኑ የተኩስ አቁም ስምምነት ምንድን ነው

ይህ ጦርነት በቅርብ ዘመናት በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ከነበሩት ከማናቸውም ግጭቶች የበለጠ ረዘም ላለ ጊዜ ሊቆይ እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ። የሃማስ ጥቃት ስፋት ያደረሰው ጉዳት ከሌላው ጊዜ የከፋ መሆኑ የዚህ ጦርነት አንዱ ልዩ ገጽታ ነው፡፡ ከእስራኤል እንጻር የተፈጸመው የቦምብ ድብደባን ተከትሎ የሟቾቹ ቁጥር መጠን ቀደም ሲል ከነበረው ማሻቀቡ ሌላው የጦርነቱ አስከፊነት ማሳያ ነው።

ላለፉት 50 ቀናት በተደረገው የእስራኤል የአየር እና የምድር ድብደባ ታይቶ የማይታወቅ ሰብአዊ ቀውስ ከተከሰተ በኋላ ሃማስ እና እስራኤል በኳታር አደራዳሪነት የተስማሙበት የአራት ቀና የተኩስ አቁም ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል።

እስራኤል ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ተኩስ አቁማ ለሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት እንድትተባበር እና ቀጠናውን ወደ ሰላም እንድትመልስ በወዳጆቿ ጭምር ብትለመንም አሻፈረኝ ስትል ቆይታለች። ይሁን እንጂ ሃማስ በያዛቸው ከ237 በላይ እስራኤላውያን ምክንያት ከዜጎቿ ከፍተኛ ግፊት እና ጫና በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ላይ በረታ፡፡ የጨቅላዎች ሞት፣ የሆስፒታሎች እና አምቡላንሶች መውደም፣ በዚህ ምክንያትም ከዓለም ማኅበረሰብ የደረሰባትን ጫና ያለሰማችው እስራኤል በሃማስ እጅ ለሚገኙ ዜጎቿ ብላ የአራት ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተቀበለች፡፡

በአሁኑ ስምምነት ሃማስ ግጭቱ ከጀመረበት ዕለት አንስቶ ከያዛቸው 237 እስራኤላውያን መካከል 50 ሲቪሎችን ለመልቀቅ፣ እስራኤል ደግሞ 150 ሴቶች እና ህጻናትን ለመልቀቅ ቃል ገብተዋል፡፡ ኳታር እንዳለችው በስምምነቱ መሰረት ሰብአዊ እርዳታም ወደ ጋዛ እንዲገባ ይደረጋል፡፡

እስራኤል በበኩሏ በሃማስ የተያዙባት 10 ተጨማሪ ዜጎቿ በተለቀቁ ቁጥር አንድ ቀን እንደምትጨምር የገለጸች ሲሆን፣ ሃማስ 10 ተጨማሪ ዜጎቿን ሲለቅ እሷ ተጨማሪ ፍልስጤማውያንን ትለቅ እንደሆነ ያለችው ነገር የለም።

ስምምነቱን አሁን ተግባራዊ መሆን የጀመረ ሲሆን፣ ምንም እንኳን ለግጭቱ ዘላቂ እልባት የሚየስገኝ ባይሆንም ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ መሻሻል እንደታየበት ተመልክቷል።

የስምምነቱ ተግባራዊነት ምን ይመስላል?

ስምምነቱ ወደ ተግባር ከመግባቱ በፊት ሃማስ እስራኤል የስምምነቱ መርሆች እየጣሰች ስለሆነ ላይሳካ ይችላል የሚል ቅሬታ ያቀረበ ቢሆንም፣ እስከ አሁን ድረስ ከሁለቱም ወገኖች እስረኞች እየተለቀቁ ናቸው፡፡

እስራኤል 39 እስረኞችን የለቀቀች ሲሆን፣ ሃማስ በበኩሉ 41 ሰዎችን ለቋል፤ ከነዚህም ውስጥ 26 የእስራኤል ዜጎች እና 15 የውጭ ዜጎች ይገኙባቸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስታወቀው በዘሬው ዕለት ስድሳ አንድ መኪናዎች ምግብ፣ ውሃ እና አስቸኳይ የህክምና ቁሳቁሶችን ለሰሜን ጋዛ አቅርበዋል። 11 አምቡላንሶች እና ሦስት የሕክምና ባለሙያዎችም ወደ አል-ሺፋ ሆስፒታል በመሄድ ለተጎዱት እርዳታ እየተደረገ እንደሆነም ድርጅቱ እስታውቋል፡፡ 129 ሺህ ሊትር ነዳጅም ወደ ጋዛ መሻገሩ ተገልጿል።

ሃማስ ስምምነቱ እንዲራዘም እንደሚፈልግ ተስፋ ሰጥቷል፡፡ የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ አባል የሆኑት ጋዚ ሃማድ ለአልጀዚራ እንደተናገሩት ሃማስ በአሁኑ ጊዜ ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመሆን ስምምነቱን ማራዘም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየሠራ ነው። “ቅድሚያ የምንሰጠው በህዝባችን ላይ የሚፈፀመውን ጥቃት ማስቆም ነው፤ ይህን የዘር ማጥፋት ዘመቻ ማስቆም እንፈልጋለን” በማለት ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።

በቀሪዎቹ ቀናት የስምምነቱ ተፈጻሚነት ምን ላይ ሊደርስ ይችላል የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ይህ የከፋው የሁለቱ ወገኖች ግጭት ወደ ተሻለ የሰላም አማራጭ ሊያመራ ይችላል የሚሉ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ ታዲያ እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉት እስራኤል እና ሃማስ እስካሁን ማንንም አሸናፊ ካላደረገው ጦርነት ተምረው ወደ ዘላቂ የሰላም ድርድር ይመጡ ይሆን ወይስ ቀን ቆጥረው ሌላ ዙር ግጭት ይቀጥላሉ? ከፖለቲካ ትርፋቸው ባሻገር የወገኖቻቸውን ስቃይ ከተመለከቱ እና ወደ ቀጣይ ሰላማዊ ድርድር ከተሸጋገሩ የሴቶች እና ህጻናት ስቃይም የሚያበቃ ይሆናል፤ በግትርነታቸው ከቀጠሉ ግን እንደከዚህ በፊቱ ሁለቱም አሸነፊ የማይሆኑበት የንጹሃን ስቃይ የሚቀጥልበት ጊዜ ይሆናል፡፡ በማይተነበየው የመካከለኛ ምሥራቅ ምስቅልቅል ውስጥ በቀጣይ የሚሆነው ጊዜው ሲደርስ እናያለን።

ለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top